በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የምርምር ማዕከል እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የምርምር ማዕከል እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የምርምር ማዕከል እየተገነባ መሆኑን የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አመራሮች በአዲስ አበባ ቃሊቲ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እየተገነባ ያለውን የምርምር ማዕከል እንዲሁም ዓለምገና የሚገኘውን ማሰልጠኛ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በጉብኝቱ በመንግሥት የተጀመረው የተቋም ሪፎርም በተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ለመመልከት ችለናል ብለዋል።
ተቋም መገንባት አገር መገንባት መሆኑን የገለጹት ሚንስትሯ ከነባር እሴቶቹ ጋር ተደምረው ተቋሙን የተሻለ ለማድረግ ትልቅ ግብዓት መሆኑን ጠቁመዋል።
ከ400 ሚለዮን ብር በላይ እየተገነባ ያለው የምርምር ማዕከል የኮንስትራክሽን ዘርፉን ኢንዱስትሪ በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
ዘርፉን ማዘመን የሚችሉ በተለይም በጥራት ተወዳዳሪነት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ በዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት መጓደል በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀርፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ከኢትዮጵያም አልፎ በምስራቅ አፍሪካ የሚጠቀስ መሆኑን የገለጹት ሚንስትሯ አጠቃላይ ዘርፉን መቀየር የሚችል አቅም የሚፈጠርበት መሆኑን አመላክተዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስትር ዴኤታ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው የምርምር ማዕከሉ በዘርፉ ያለውን ችግር በአግባቡ የሚለይ መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ በአጠቃላይ ያሉ ውስንነቶችን እንዲሁም የብቁ ባለሙያ እጥረትን በመቅረፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አክለዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ በቀለ በምርምር የታገዙ ሥራዎች ከወጭ አንጻር በርካታ ጥቅም እንደሚያስገኙ ገልጸዋል።
በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በማእከሉ የሚገነባው ላቦራቶሪም ለጎረቤት አገራት ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ነው ያመላከቱት።