በአማራ ክልል አሳታፊ የሽምግልና ሥርዓትን አጎልብቶ በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል አሳታፊ የሽምግልና ሥርዓትን አጎልብቶ በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እየተሰራ ነው
መተማ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 በአማራ ክልል አሳታፊ የሽምግልና ሥርዓትን አጎልብቶ በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
ምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ በግጭት አፈታት፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመለየት፣ በቀልን በመከላከልና በሰላም ግንባታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የዕቅድና በጀት ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ቢያዝን መሰለ በመድረኩ እንደተናገሩት፣ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እያንዳንዱ ግለሰብ ከራሱ የሚጠበቀውን ለይቶ መስራት ይጠበቅበታል።
ሁሉን አቀፍ እይታ በመያዝ መሰረታዊ ችግርን ከመፍታት ባለፈ ዘላቂ የሰላም ግንባታን መከተል እንደሚገባ ገልፀዋል።
ለዘላቂ ሰላም በእጅ ያለውን አቅም መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት አቶ ቢያዝን፣ ለዚህም አሳታፊ የሽምግልና ስርዓትን በማጎልበት ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአካባቢው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ግጭቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ "በግጭቱ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የተሳተፉ ታጣቂዎች በሀገራዊ የሽምግልና ሥርአት መሰረት እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል" ብለዋል።
በተሰራው ሥራ መንግስት የሰጠውን የሰላም አማራጭ ተጠቅመው በምዕራብ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ይንቀሳቀሱ የነበሩ 437 ታጣቂዎች እጃቸውን መስጠታቸውን ገልፀዋል።
እነዚህን ወገኖች ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል የበደሉትን ህዝብ በልማት እንዲክሱ ለማድረግ ተባብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የፀጥታ አካሉ ለዘላቂ የሰላም ግንባታ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፣ "ለእዚህም የክልሉ መንግስት ተገቢውን እገዛ ያደርጋል" ሲሉ አረጋግጠዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አሰፋ ሸቤ በበኩላቸው፣ በዞኑ ያለውን ሰላምና ፀጥታ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ ነው።
መንግስት የሰጠውን የሰላም አማራጭ ተጠቅመው በዞኑ 122 ታጣቂዎች እጃቸውን በሰላም መስጠታቸውን ተናግረዋል።
"በሰላም እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎችን ከበደሉት ህዝብ ጋር በሀገር ሽምግልና ባህል መሰረት በማስማማት ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩና በልማት እንዲሳተፉ ይደረጋል" ብለዋል።
በአካባቢያቸው በነበረ የጸጥታ ችግር ከቀበሌ ወደቀበሌ በነጻነት ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ እንደነበር የገለጹት ደግሞ ከአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ መጥተው በመድረኩ የተሳተፉት አቶ ዳገት ከፋለ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ለታጣቂዎች በተደረገ ምህረት እጃቸውን ለመንግስት በሰላም መስጠታቸው አርሶ አደሩ በሰላም ወጥቶ እንዲገባና የልማት ሥራዎችን ያለስጋት እንዲያከናውን ማስቻሉን ገልጸዋል።
ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ ሊቀ ካህናት አባይነህ አማረ መንግስት የጀመረውን የሰላም ጉዞ ዳር ለማድረስ የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
"የተገኘውን ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ህዝብን መበደላቸውን አምነው ለይቅርታ እስከመጡ ድረስ ተበዳይ ይቅር ባይ ስነልቦና በመያዝ ይቅርታውን ማፅናት ይኖርበታል" ብለዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መድረክ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።