ቀጥታ፡

ኅብረተሰቡ በመጪው የገና በዓል በተመጣጣኝ ዋጋ የምርት አቅርቦት እንዲያገኝ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 በአዲስ አበባ ኅብረተሰቡ በመጪው የገና በዓል በተመጣጣኝ ዋጋ የምርት አቅርቦት እንዲያገኝ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ።

የመዲናዋ ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ መጪውን በዓል ምክንያት በማድረግ በተደረገው ዝግጅት ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።   

ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር እንደገለጹት፤ መጪው ገናን ምክንያት በማድረግ ለኅብረተሰቡ ምርቶችን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።

በተለይም የምርት አቅርቦትን ለማስፋትና አማራጭ ገበያዎች ጥቅም ላይ ለማዋል በከተማ አስተዳደሩ የተቋቋመው የኢኮኖሚ ክላስተር ኮሚቴ ወደ ሥራ መግባቱን ነው የገለጹት።

በዚህም ምርት ከየት ይገኛል?፣ መቼ ይቀርባል?፣ ማኅበራት ምን ያህል ያቀርባሉ? በሚለው ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።    

ይህንንም ተከትሎ፤ በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ በተለያዩ ሥፍራዎች መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ጨምሮ የተለያዩ የእንስሳት ውጤቶች እየቀረቡ መሆኑን አብራርተዋል።     

በተለይም ደግሞ የሸማች ማኅበራት ምርቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደሩ በመረከብ ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።  

ማኅበራት በተለይም ዶሮና እንቁላሎችን በራሳቸው ከሚያቀርቡት ባሻገር ከኤልፎራ ጋር በመተባበር የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር የሚያግዝ አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።  

ከዚህ በፊት በመዲናዋ ገበያውን ለማረጋጋት የተቋቋሙት የእሁድ ገበያዎችም ለመጪው ገና በዓልም ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።     

አሁን ላይ በከተማዋ በተለያዩ ሥፍራዎች 126 እሁድ ገበያዎች ለበዓል የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑም ገልጸዋል።    

የበዓል ገበያው እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ እንዲሁም ባዕድ ነገር በመቀላቀል አላግባብ ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይም የቁጥጥርና ክትትል እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቅኝት ባደረገባቸው የመዲናዋ አካባቢዎች ለበዓል የሚያስፈልጉ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን ታዝቧል።   

ቦሌ ክፍለ ከተማ ጅምላ ምርት ካቀረቡት መካከል ወጣት ምስክር ወዳጄ እንደገለጸው ለመጪው ገና ለኅብረተሰቡ ሽንኩርት፣ ቲማቲም የመሳሰሉ ምርቶች በዝቅተኛ ዋጋ አቅርበናል ብሏል።

ሸማቾች በበኩላቸው ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት ሁኔታዎች መመቻቸቱ ትልቅ ሥራ መሆኑን ጠቁመው ዘላቂነቱ ላይ ትኩረት እንዲደረግም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም