ቀጥታ፡

በቀጣይ ጥር ወር በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ ፤ፀሀያማና ነፋሻማ የአየር ጠባይ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሚቀጥለው አንድ ወር በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ ፤ፀሀያማ እና ነፋሻማ የአየር ጠባይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው ጋዜጣዊ  መግለጫ በሚቀጥለው አንድ ወር በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ ፤ፀሀያማ እና ነፋሻማ የአየር ፀባይ ሁኔታ እንደሚጠበቅ ገልጿል፡፡

በአንዳንድ የሀገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች ማለዳ እና ሌሊት ቀዝቃዛ የአየር ፀባይ ሁኔታ እንደሚኖር ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል  በጅማ ፤ኢሉአባቦራና የምዕራብ ወለጋ ዞኖች ፤በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አንዳንድ አከባቢዎች የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፤በሲዳማ ክልል እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ በመግለጫው ተመላክቷል ፡፡

በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቃማ የአየር ሁኔታ የሚያስተናግድ መሆኑ ለሰብል ስብሰባ የራሱ የሆነ በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ኢንስቲትዩት ገልጿል፡፡

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚኖረው ደረቃማ የአየር ጠባይ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ደጋማ ቦታዎች ላይ ቀጣይነት ያለው ቅዝቃዜ እንደሚስተዋል ተመላክቷል፡፡

ቅዝቃዜውም እድገታቸውን ሙሉ በሙሉ ባልጨረሱ ሰብሎች ፤በመስኖ በመታገዝ የሚለሙ የፍራፍሬ ተክሎችና የጓሮ አትክልቶች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ይጠበቃል ፡፡

ለዚህም አርሶ አደሮች እንደ የአካባቢያቸው ነባራዊ የአየር ጠባይ ሁኔታ ቅዝቃዜውን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም በሰሜን ምስራቅ ፤በምስራቅ ፤በመካከለኛው ደቡብ፣ ደቡብ ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደቡባዊ ክፍል እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡

ይህም በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አርብቶአደር አካባቢዎች የመጠጥ ውሃና የግጦሽ ሳር አቅርቦትን የሚያሻሻል እንደሆነም እንደዚሁ፡፡

የላይኛው ባሮ አኮቦ፤የመካከለኛው እና የታችኛው ስምጥ ሸለቆ ፤ኦሞ ጊቤ ፤መካከለኛው ገናሌ ዳዋ ፤ዋቢ ሸበሌ እንዲሁም የመካከለኛው አባይ ተፋሰሶች አንዳንድ ጊዜ ከመጠነኛ እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት የሚያገኙ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ቀሪዎች በሀገሪቱ የሚገኙ ተፋሰስ አካባቢዎች ደረቅ እና ከፊል ደረቃማ የአየር ጠባይ ሁኔታን የሚያስተናግዱ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም