ቀጥታ፡

መንግስት ከአገልግሎት ውጭ በሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ሽያጭ ዋጋ እንዲሻሻል ወሰነ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 መንግስት ለብረት አምራች ፋብሪካዎች የግብዓት እጥረትን ለመቅረፍ ከአገልግሎት ውጭ በሆኑ በቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ሽያጭ ዋጋ እንዲሻሻል ወሰነ።

የገንዘብና የማዕድን ሚኒስቴሮች ባወጡት የጋራ መግለጫ የብረት አምራች ፋብሪካዎች የግብዓት እጥረትን ለመቅረፍ ከአልግሎት ውጪ በሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ሽያጭ ላይ የዋጋ ማሻሻያ መደረጉን ይፋ አድርገዋል።

የዋጋ ማሻሻያ የተደረገውም ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎቹ ከትራንስፖርት እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ጋር በተያያዘ የዋጋ ማሻሻያ እንዲደረግላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ነው።

የዋጋ ማሻሻያውም ፋብሪካዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥሬ ዕቃ እንዲያገኙ፣ ምርታማነታቸው እንዲጨምርና የመንግስት የውጭ ምንዛሬ ወጪ በማስቀረት እንደሚያግዝ ተገልጿል።

በዚህም አዲስ አበባ በ100 ኪ.ሜ ራዲየስ ከሚገኙ መስሪያ ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪዎች መግዣ ዋጋ ይፋ አድርጓል።

ሙሉ መግለጫውም እንደሚከተለው ቀርቧል።

ከአገልግሎት ውጪ በሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪች ሽያጭ ላይ የተደረገ የዋጋ ማሻሻያ

የብረት አምራች ፋብሪካዎች የግብአት እጥረትን ለመቅረፍ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የማዕድን ሚኒስቴር በጋራ በተለያዩ የፌደራል መንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የሚገኙ ቁርጥራጭ ብረታብረቶች፣ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪች ለብረት አምራቾች የገንዘብ ሚኒስቴር በሚወስነው ዋጋና የማዕድን ሚኒስቴር በሚደለድለው የብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ኮታ መሰረት በሽያጭ እንዲቀርቡ ተወስኖ ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል፡፡

እስከ አሁን ደረስም የተለያዩ ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ቁርጥራጭ ብረቶቹን እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ከአፈጻጸም ጋር በተያያዘም ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎቹ ከትራንስፖርትና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ጋር በተያያዘ የዋጋ ማሻሻያ እንዲደረግላቸው ለማዕድን ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት አግኝተዋል።

የመንግስት ዋነኛ አላማ የሽያጩ ዋና መነሻ ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥሬ ዕቃ እንዲያገኙ፣ ምርታማነታቸው እንዲጨምር እንዲሁም መንግስት ያወጣው የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ለማሰቀረት በመሆኑ የአምራች ፋብሪካዎቹን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የዋጋ እና ሌሎች ወጪዎች ማሻሻያ ተደርጓል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ለፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች፣ ለመንግስት የልማት ድጅቶች እና ለሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ታህሣሥ 24 /2015 ዓ.ም በላከው ደብዳቤ መሰረት ከአገልግሎት ውጪ በሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች ፣ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪች ሽያጭ ላይ የዋጋ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡

በዚህም መሰረት ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ከአዲስ አበባ በ100 ኪ.ሜ ዙሪያ ውስጥ ከሚገኙ መስሪያ ቤቶች ውጭ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪች ሲገዙ በሚከተለው የዋጋ ተመን የሚገዙ መሆኑ ታውቆ፤

  1. ስቲል ስክራፕ ብረት የቀድሞ ዋጋ ለአንድ ኪ/ግ 64.00 ሲሆን የተሻሻለው የአንድ ኪ/ዋጋ 48.00
  2. ካስት አይረን የቀድሞ ዋጋ ለአንድ ኪ/ግ 51.75 ሲሆን የተሻሻለው የአንድ ኪ/ዋጋ
    35.00
  3. ስክራፕ ተሽከርካሪ እና ማሽነሪዎች የቀድሞ ዋጋ ለአንድ ኪ/ግ 51.25 ሲሆን የተሻሻለው የአንድ ኪ/ዋጋ 39.00
  4. የአልሙኒየም ስክራፕ የቀድሞ ዋጋ ለአንድ ኪ/ግ 120.00 ሲሆን የተሻሻለው የአንድ ኪ/ዋጋ 90.00
  5. ያገለገለ የተሸከርካሪ/ማሽነሪ መለዋወጫ የቀድሞ ዋጋ ለአንድ ኪ/ግ 51.25 ሲሆን የተሻሻለው የአንድ ኪ/ዋጋ 39.00

አቅላጭ ፋብሪካዎች ከአዲስ አበባ ከ100 ኪ.ሜ ርቀት በላይ (ከ100 ኪ.ሜ ራዲየስ ውጪ) ከሚገኙ መስሪያ ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች ፣ ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪች ሲገዙ ከላይ የተጠቀሰው የዋጋ ማሻሻያ እንደተጠበቀ ሆኖ ከታች የተዘረዘሩት ወጪዎች ተቀናሽ የሚደረጉ ይሆናሉ።

 አንድ ኪሎ ስክራፕ ብረት ለመቁረጥ፣ ለመለየት፣ ለመሰብሰብ ብር 5.80 /አምስት ብር ከ80/100/

 አንድ ኪሎ ስክራፕ ብረት ለማስጫን ብር 2.50 /ሁለት ብር ከ50/100/

 ለትራንስፖርት ለአንድ ኪሎ ሜትር ብር 0.009534 ተቀናሽ እንደሚደረግ ተወስኗል።

ስለሆነም አዲስ የተሻሻለው የስክራፕ የመሸጫ ዋጋ መሰረትም የማእድን ሚኒስቴር ለሚመድባቸው ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ብቻ ያለተጨማሪ እሴት ታክስ ያለ ጨረታ እንዲሸጥ ፣ እንዲሁም በጨረታ ሂደት ላይ የሚገኝ የየትኛውም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወይም የመንግሥት ተቋማት የጨረታ ሂደቱ ተቋርጦ አሁን መንግስት ስራ ላይ እንዲውል በወሰነው መሰረት የሚከናወን ይሆናል።

የገንዘብ ሚኒስቴር

የማዕድን ሚኒስቴር

አዲስ አበባ


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም