ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በጤና፣ በንግድና አካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ያላቸውን 1 ሺ 35 ደረጃዎችን አጸደቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲቱዩት ከጤና፣ ከአካባቢ ጥበቃና ንግድን ከማቀላጥፍ አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ያላቸውን 1 ሺ 35 ደረጃዎች ማጽደቁን አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ ደረጃዎችን እንዲያዘጋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ዓለም አቀፍ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ያላቸውን ደረጃዎች ማጽደቁን ገልጿል፡፡

ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሔደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባ በ7 ዘርፎች እና በ25 የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተዘጋጅተው ከቀረቡት 1 ሺ 37 ደረጃዎች ውስጥ 1 ሺ 35 ደረጃዎችን መርምሮ አጽድቋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በቀለ፤ የጸደቁት ደረጃዎች ኢኮኖሚን ከማሳደግ፣ የሰውና የእንስሳት ደህንነት ከማረጋገጥ፣ ከአካባቢ ጥበቃና ንግድን ከማቀላጠፍ አኳያ ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የንግድ ተወዳዳሪነት አቅምን ለማጎልበትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማከናወን እንደሚረዳ ነው የተናገሩ።

ዶክተር መሰረት የደረጃው መጽደቅ የሸማቾችን ጥቅም ከማስጠበቅና የቁጥጥርና ክትትል ተግባራትን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጠርም ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ አስገዳጅ ደረጃዎች በትክክል ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል የክትትልና ድጋፍ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተው ደረጃዎቹ በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ፣ በኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች፣ በምግብና ግብርና ውጤቶች እንዲሁም በመሰረታዊ አጠቃላይ ደረጃዎች ተሰጥተዋል ብለዋል፡፡

በኮንስትራክሽንና ሲቪል ምህንድስና፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል እና በአካባቢ ጤና ዘርፍ የተሰጡ ደረጃዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዶክተር መሰረት ከነዚህ ውስጥ በኮንስትራክሽን፣ በአካባቢ እና ጤና ደህንነት፣ በዘይትና በለስላሳ መጠጥ እንዲሁም በኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፍ 32 ደረጃዎች በአስገዳጅነት የጸደቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም