ቀጥታ፡

ከ43 ሚሊዮን ሊትር በላይ የፓልም የምግብ ዘይት ግዢ ተፈጽሟል- የገንዘብ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሣሥ 25/2015 ከ43 ሚሊዮን ሊትር በላይ የፓልም የምግብ ዘይት ግዢ መፈጸሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የምግብ ዘይት አንዲያገኝ ለማስቻል ጅቡቲ ከሚገኘው ጎልደን አፍሪካ ካምፓኒ የ43 ሚሊዮን 37 ሺ 412 ሊትር የፓልም የምግብ ዘይት ግዢ መፈጸሙን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

የግዢ ውሉን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት መሆናቸውም ተጠቁሟል።

ለግዢ የሚውለውን የ69 ሚሊዮን 894ሺ 440 የአሜሪካን ዶላር ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋስትና የሰጠው የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑም ሚኒስቴሩ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡

የምግብ ዘይቱ ግዢ በአንድ አመት የክፍያ ጊዜ የሚፈጸም ሲሆን ይህን የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ዋጋን ለማረጋጋት ታስቦ የተፈጸመ ግዢ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል።

ሚኒስቴሩ ለኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት በላከው ደብዳቤም በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ እሽግ የፓልም ምግብ ዘይት የመሸጫ ዋጋ እንደሚከተለው አሳውቋል፡-

በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ የፓልም ምግብ ዘይት መሸጫ ዋጋ

• ባለ 3 ሊትር በጄሪካን …… ብር 314

• ባለ 5 ሊትር በጄሪካን …… ብር 510

• ባለ 20 ሊትር በጄሪካን …… ብር 2003 መሆኑም አስታውቋል።

ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ከተሞችን በተመለከተም ርቀትን ታሳቢ በማድረግ የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ታሪፍ በኩንታል 60 ሳንቲም በአንድ ኪ.ሜ መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ ሽያጭ እንዲከናወን ገልጿል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርም በተለመደው መልኩ የክልልና የከተማ አስተዳደሮችን የስርጭት ኮታ በመመደብ ለኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት እዲያሳውቅ አቅጣጫ ተቀምጧል ብሏል የገንዘብ ሚኒስቴር በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም