ኢትዮጵያን ለማበልጸግ የሚደረገውን ጥረት ምሁራን በጥናትና ምርምር መደገፍ ይጠበቅባቸዋል-ዶክተር ፍፁም አሰፋ

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 ኢትዮጵያን ለማበልጸግ የሚደረገውን ጥረት ምሁራን በጥናትና ምርምር መደገፍ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ ተናገሩ።

ኢትዮጵያን በሰላም፣ በልማትና በብልፅግና ማማ ላይ ለማድረስ ምሁራን በጥናትና ምርምር የታገዘ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ነው ዶክተር ፍፁም የገለጹት።

በሀገረ መንግስት ግንባታና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክረው ሁለተኛው ዙር የምሁራን ውይይት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ ኢትዮጵያን ከችግር ለማላቀቅ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የምሁራን ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ላይ በርካታ የለውጥ አጋጣሚዎች ቢስተዋሉም በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ባለመፈጠሩ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጠረው ሀገራዊ ለውጥ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ኢትዮጵያን ወደ ታላቅነት ለማሻገር በተቋማት አደረጃጀቶችና በህብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በተቃራኒው ደግሞ ሀገራዊ ለውጡ እንዲቀለበስ ከውስጥም ከውጭም በርካታ መሰናክሎች ማጋጠማቸውን አስታውሰው፤ በመላው ኢትዮጵያውያን የተቀናጀ ጥራትና ትብብር ለውጡን ማስቀጠል መቻሉን አስረድተዋል።

በመሠረታዊ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ብሎም ኢትዮጵያን በሰላም፣ በልማትና በብልፅግና ማማ ላይ ለማድረስ የሚከናወኑ ተግባራትን ምሁራን በጥናትና ምርምር የታገዘ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ከድህነት መውጫው ብቸኛው መንገድ በሀገር በቀል እውቀቶችና ጥበቦች የታገዘ ዘመናዊ የትምህርት ስርዓት ማስፈን መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ውይይቱ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሮ የተሻለችና በዕድገት ጎዳና የምትጓዝ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማመቻቸት እንደሆነ አብራርተዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዑባህ አደም፤ ውይይቱ የሀገርን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ በስኬት ዳር እንዲደርስ ያግዛል ብለዋል።

ምሁራን "በሀገረ መንግስት ግንባታ -የምሁራን ሚና" በሚል በቀረበ ሰነድ ላይ እየመከሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም