የዓለም ባንክ ለጤና ተደራሽነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ ለጤና ተደራሽነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገውን ሙያዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በሰራችው ስራ ላይ ላደረገው ትብብር ከጤና ሚኒስቴር እውቅና ተሰጥቶታል።
እውቅናውን የተቀበሉት በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የጤና ምጣኔ ሃብት ባለሙያ ጸጋነህ አምሳሉ፤ ለኢዜአ እንደተናገሩት የጤናውን ዘርፍ ለመደገፍ ባንኩ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ይሰራል።
ባለፉት አስር ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጤና መድኅን መርሃ-ግብር ሙያዊና ሌሎች ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ባንኩ ላደረገው አስተዋጽኦ እውቅና በመስጠቱ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ይረዳል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎትን በማስፋት አምራችና ጤናማ ዜጋን በመፍጠር የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የያዘችውን ግብ ለማሳካት ባንኩ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ ባንኩ በቀጣይ አራት ዓመታት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለጤና መድህን የቴክኒክ ድጋፎችን ያደርጋል።
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ከጀመረችው ለውጥ ውስጥ ፍትሃዊና አካታች የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ማዳረስ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ደግሞ የጤና መድህን አገልግሎት አንዱ ነው።
የጤና መድህን ዜጎች ለጤና አገልግሎት በሚያወጡት ወጪ ምክንያት ለድህነት እንዳይዳረጉ እንዲሁም የገንዘብ አቅም ባለመኖሩ የጤና አገልግሎት ሳያገኙ እንዳይቀሩ ያደርጋል።
አገልግሎቱ ባለፉት አስር ዓመታት ተግባራዊ በመደረጉ ከ45 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።