ቀጥታ፡

በመሪነት ዘመን ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ሰርቶ ማለፍ ዘላለማዊ ክብርና ኩራት ነው- የበጎ ሰው ተሸላሚ አቶ ግርማ ወንድአፍራሽ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 በመሪነት ዘመን ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ሰርቶ ማለፍ ዘላለማዊ ክብርና ኩራት በመሆኑ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ለዚህ ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ የበጎ ሰው ተሸላሚው አቶ ግርማ ወንድአፍራሽ ተናገሩ።

በታሪክ አጋጣሚ ያገኙትን የመሪነት ዕድል በቅጡና በልኩ ተወጥተዋል፤ የ82 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ እና የበጎ ሰው ተሸላሚው ግርማ ወንድአፍራሽ።

አቶ ግርማ ወንድአፍራሽ ለሽልማት ሲጠየቁ "በሽልማቴ ፈንታ ድልድይ ይሰራልኝ" በማለት የሕዝብ አለኝታነታቸውን በተግባር ያሳዩ ታላቅ የሀገርና የሕዝብ ባለውለታ በመሆን ስማቸው በብዙዎች ዘንድ ይነሳል።

እርሳቸው በተወለዱበት ቀዬ፣ ባደጉበት መንደርና በመሩት ሕዝብ መሀል እንደስማችው የገዘፈው ግርማ ዛሬም አብሯቸው ዘልቋል።

በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሀገር መንዝ አውራጃ አንጾኪያ ገምዛ ወረዳ የተወለዱት አቶ ግርማ ወንድአፍራሽ፤ በሰሜን ሸዋ ወረዳዎች ተዘዋውረው በአስተዳዳሪነት ለረዥም ዓመታት መርተዋል።

ባገለገሉባቸው ቦታዎችና ወቅቶች የመሪነትን ልኬት በግብር የገለጹ፣ ዛሬም ሕያው የሆኑ ዘመን ተሻጋሪ አሻራቸውን አትመዋል።

በተለይም በተወለዱባት አንጾኪያ ገምዛ ወረዳ በአስተዳዳሪነት በቆዩባቸው ስምንት ዓመታት የልማት አሻራቸው ለመሪዎች ሁሉ አርዓያ ተደርጎ ይወሳል።

በማምሻ ዕድሜያቸው ኑሯቸውን በአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ ከተማ በሆነችው መኮይ ያደረጉት አቶ ግርማ፤ በነዋሪው ተከብረው እና ተወደው ይኖራሉ።

ለምን? ቢሉ የአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ እና አካባቢው ሕዝብ ዕውቀት የገበየው፣ ርሀቡን ያስታገሰው፣ ኑሮውን ያሻሻለው፣ ተዘዋውሮ ግብይት የሚፈጽመው በአቶ ግርማ የልማት አሻራዎች ነውና።

የኢዜአ ሪፖርተር በትውልድ መንደራቸው ተገኝቶ ያነጋገራቸው አቶ ግርማ ወንድአፍራሽ፤ በዘመናቸው ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት ቤት፣ አራት ጤና ጣቢያዎች፣ መንገድና ሌሎች መሰረተ-ልማቶችን ማሰራታቸውን ያስታውሳሉ።

ይህም “ያልተማረ ሕዝቤ ዕውቀት እንዲገበይ፣ ከበሽታ እንዲፈወስና እንዲያመርት መሰረተ-ልማት በመገንባት የተቻለኝን አድርጌያለሁ፤ ፈጣሪም አግዞኛል” ይላሉ።

ሌላው በጉልህ የሚጠቀሰው ሚናቸው በአስተዳዳሪነት ዘመናቸው በ1977 ዓ.ም የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ሕዝባቸው በድርቁ ክፉኛ ተጎድቶ፣ በርሀብ አለንጋ ሲገረፍ፣ ህፃናት በሞት ሲረግፉ የታደጉበት ጥበብ ነው።

በወቅቱ አካባቢው የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ መልክዓ ምድር በመሆኑ አቶ ግርማ የወቅቱን የወርልድ ቪዥን ኃላፊ አየር ማረፊያ ቢኖር እንደሚረዱ ስለገለጹላቸው፣ 3 ሺህ 600 ሰዎችን በማስተባበር በአንድ ቀን ጊዜያዊ የአውሮፕላን ማረፊያ አሰርተው ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ አድርገዋል።

በወቅቱ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የአውሮፕላን ማረፊያ በማሰራታቸው የወርልድ ቪዥን ኃላፊ ለሽልማት ሲጠይቃቸው "በሽልማቴ ፈንታ የቦርከና ወንዝ ድልድይ ይሰራልኝ " በማለት ድልድዩ ተሰርቶ ዛሬም ድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

በድርቅ ወቅት ወላጆቻቸውን ያጡ በርካታ ህፃናት ‘አባታቸው ግርማ፣ እናታቸው ኢትዮጵያ’ ተብለው በአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጉዲፈቻ እንዲሰጡ አድርገዋል።

ወድቆ የተገኘን ህፃንም ባለቤታቸው አጥብተው እንዲያሳድጉ ያደረጉት አቶ ግርማ ወንድአፍራሽ ታትሮ መሥራትን፣ ለሕዝብ ተጨባጭ ለውጥ ፋና ወጊነትና ከሰብዓዊነት ጋር አጣምረው ሰርተዋል።

በአካባቢው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቆሙ በማድረግ ማኅበረሰብ እንዲሰለጥን በጎ ሚናም ተወጥተዋል።

ከከሚሴ እስከ መኮይ የመኪና መንገድ፣ የቦርከና ወንዝ ድልድይ፣ ለእርዳታ አውሮፕላን ማረፊያ በማሰራት ሕዝባቸውን ከተጨማሪ እልቂት ታድገዋል።

በዚህ አኩሪ ታሪካቸውም በ2011 ዓ.ም የ7ኛው ዙር በመንግሥት ተቋማት ኃላፊነት ዘርፍ የበጎ ሰው ተሸላሚ መሆን የቻሉ ታላቅ የሕዝብ ባለውለታ ናቸው።

በሦስት ሥርዓተ-መንግሥታት ውስጥ ያለፉት አቶ ግርማ፤ “ሁሉም ነገር አላፊ ነው፤ በመሪነት የተሰየሙ ግለሰቦች ከግል ጥቅም ይልቅ ወገንን የሚያግዝ፣ አገርን የሚለውጥ ሥራ መሥራት ይገባቸዋል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዚህ ወቅት እንደ አገር የተጀማመሩ በምግብ ራስን የመቻል እንቅስቃሴዎችን አድንቀው፤ በተለይም በስንዴ ረጂነት ሰበብ ጫና የሚያደረጉ የውጭ ኃይሎችን ተጽዕኖ ለመቋቋም ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሕዝቡ በሁሉም አካባቢዎች በሰላም አምርቶ የሚኖርበት ድባብ ሊፈጠርም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም