ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን ጉዳት የደረሰባቸው 100 የመጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠግነው ለአገልግሎት በቅተዋል-የዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ

ደሴ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 በደቡብ ወሎ ዞን በተለያየ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው 100 የመጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠግነው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የመጠጥ ውሃ ግንባታና ጥገና ባለሙያ ንጉስ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በጦርነትና በአገልግሎት ብዛት ለብልሽት የተዳረጉ የመጠጥ ውሃ ተቋማት መልሶ በመጠገን ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ ነው።

እስካሁን 100 የመጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠግነው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አንስተው በዚህም 72 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማቱን መልሶ ለመጠገን 40 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉንና ከጥገናው በተጨማሪም የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋኑን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በበጀመት ዓመቱ 180 አነስተኛና መካከለኛ መጠጥ ውሃ ተቋማትን በአዲስ የመገንባት ስራ መጀመሩንም የገለጹት ባለሙያው  ለውሃ ተቋማቱ ግንባታ 82 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን አንስተዋል።

ተቋማቱ እስከ መጪው ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ተጠናቀው ወደስራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ለአገልግሎት ሲበቁም 48 ሺህ ሰዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችሉም አመልክተዋል።

የወረባቦ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ፋጡማ ሙሳ ቀደም ሲል ይጠቀሙበት የነበረው የመጠጥ ውሃ ተቋም በጦርነቱ ጉዳት ደርሶበት አገልግሎት በማቆሙ ለመጠጥ ውሃ ችግር ተጋልጠው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

አሁን መልሶ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ተደስተናል፣ ችግራችንንም አቃሎልናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ሌላዋ የቢስቲማ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሐዋ ሰይድ በበኩላቸው የውሃ ተቋሙ መልሶ ተጠግኖ ለአገልግሎት መብቃቱ በውሃ ፍለጋ ይገጥማቸው የነበረውን ድካምና እንግልት ማስቀረቱን ተናግረዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን የመጠጥ ውሃ ሽፋን 54 በመቶ መሆኑን የዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም