ቀጥታ፡

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መሪው አርሰናል ከኒውካስትል ዩናይትድ የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሊጉ መሪ አርሰናል ከኒውካስትል ዩናይትድ ጋር ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 4 ሰአት ከ45 በኤምሬትስ ስታዲየም ይከናወናል።

አርሰናል በ43 ነጥብ ፕሪሚየር ሊጉን በመምራት ላይ ሲሆን ኒውካስትል ዩናይትድ በ34 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ሲገናኙ ዛሬ የሚያደርጉትን ጨምሮ ለ55ኛ ጊዜ ነው።

አርሰናል 33 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ኒውካስትል ዩናይትድ ደግሞ 11 ጊዜ አሸንፏል።

10 ጊዜ አቻ ወጥተዋል።

በ54ቱ ጨዋታዎች አርሰናል 90 እንዲሁም ኒውካስትል ዩናይትድ 43 ግቦችን ማስቆጠራቸውን የቢቢሲ መረጃ ያሳያል።

አርሰናል ከኒውካስትል ዩናይትድ ጋር በሜዳው ያደረጋቸውን ያለፉት 11 ጨዋታዎች አሸንፏል።

በ2021/22 የውድድር ዓመት ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል።( ሁለቱም ያሸነፉበት በተመሳሳይ 2 ለ 0 ነበር)

ኒውካስትል ዩናይትድ አርሰናልን በፕሪሚየር ሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ በኤምሬትስ ያሸነፈው እ.አ.አ በ2010/11 የውድድር ዓመት ነበር።

አንዲ ካሮል ባስቆጠረው ግብ የለንደኑን ክለብ 1 ለ 0 አሸንፏል።

የ39 ዓመቱ እንግሊዛዊ አንዲ ማድሌይ የሁለቱን ክለቦች ተጠባቂ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

በሌሎች የ19ኛ ሳምንት መርሐግብሮች ማንችስተር ዩናይትድ ከቦርንማውዝ፣ ኤቨርተን ከብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን እና ሌይስተር ሲቲ ከሳውዝሀምተን በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰአት ከ45 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም