በጋምቤላ ክልል የኢንተርፕራይዝ ልማቱን ለማጠናከር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናከሮ ይቀጥላል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የኢንተርፕራይዝ ልማቱን ለማጠናከር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናከሮ ይቀጥላል ተባለ
ጋምቤላ፣ ታህሳስ 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኢንተርፕራይዝ ልማቱን ለማጠናከር የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፉን ለማጠናከር ለክልሉ ከፍተኛ የአመራር አካላት በጋምቤላ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ እንዳሉት፤ የኢንተርፕራይዝ ልማቱን በማስፋት በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ልማት ለመለወጥ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ በትኩረት ይሰራል።
ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩ ስኬት እውን መሆን የአምራች ኢንተርፕራይዞች ልማት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው፤ የአምራች ኢንዱስትሪው መስፋት ከኢኮኖሚያዊ እድገቱ ባሻገር የስራ እድልን ለመፍጠርም አስተዋፆው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ይህንም ታሳቢ በማድረግ የአምራች ኢንተርፕራይዞችን ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ለተግባራዊነቱ ሰፊ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በመሆኑም የኢንተርፕራይዝ ልማቱን በማስፋት የክልሉ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ልማት ለመቀየር እየተካሄደ ላለው ጥረት መሳካት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
በዕለቱ የተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የአምራች ኢንተርፕራይዞች በሚሰፉበትና በሚጠናከሩበት ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ አቋም ለመያዝ ያለመ መሆኑን ዶክተር አለባቸው አስገንዝበዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኩዋይ ጆክ በበኩላቸው ለሚደረገው ኢኮኖሚያዊ ሽግግር መሳካት የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪው መስፋት የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በተለይም እንደ ሀገር የኢኮኖሚ ብልጽግናን ለማምጣት እየተሰራበት ያለው አንዱ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ዘርፉን በማጠናከርና በማስፋት ረገድ የክልሉ መንግስት በተናበበና በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ለስኬታማነቱም በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተጀመረው ድጋፍና ትብብር እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
ካሁን በፊት በክልሉ ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ በዘርፉ የተሰማሩት ባለሃብቶች ውስን መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቡን ዌው ናቸው።
በመሆኑም በዘርፉ ያለውን ግንዛቤ በማጠናከር የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ዘርፉን ለማስፋትና ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።