ቀጥታ፡

አየር መንገዱ ወደ ሽሬ በረራ መጀመሩ ከቤተሰቦቻችን ጋር ዳግም እንድንገናኝ በማድረግ ልዩ ደስታ ፈጥሮልናል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 24/2015 አየር መንገዱ ወደ ሽሬ በረራ መጀመሩ ከቤተሰቦቻችን ጋር ዳግም እንድንገናኝ በማድረግ ልዩ ደስታ ፈጥሮልናል ሲሉ መንገደኞች ተናገሩ።

መንግስትና ህወሓት በደቡብ አፍሪካና ኬንያ የደረሱትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እያደረሰ ነው፤ የትራንስፖርትና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችም ዳግም ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ መቀሌ ዳግም በረራ የጀመረ ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የሽሬ በረራ አስጀምሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ "T-400" አውሮፕላን ሽሬ እንዳስላሴ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም የተወሰኑ መንገደኞች መሬት አየሳሙ የደስታ እንባ ሲያነቡ ሌሎቹ ህልም የመሰለውን እውነት ለመጋፈጥ በር ላይ ወደሚጠብቋቸው ቤተሰቦቻቸው አመሩ፡፡

ሀሴት በተሞላበት ደስታም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቃቅፈው አነቡ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው መንገደኞችም አየር መንገዱ ዳግም በረራ መጀመሩ ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ነው የተናገሩት፡፡

"አራስ ሚስቴን፣ ጨቅላ ልጄን ተለይቼ መኖር ከጀመርኩ ከሁለት ዓመት በላይ አስቆጠርኩ" ሲልም ነው ያነጋገርነው መንገደኛ አስተያየቱን የሰጠው፡፡

"ስሜቱ ከባድ ነው፣ ሰላም ማለት ከመለያየት በኋላ መገናኘት፣ ተስፋ የቆረጡክበት ጉዳይ ወደ ብስራት ሲቀየር የሚሰማህ ስሜት ማለት ነው።" ይላል

ሰላም የሁሉም ማጠንጠኛ የሁሉም መሰረት ነው የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ፣ የሰላም ስምምነቱ ለመላ ኢትዮጵያውያን እፎይታን የፈጠረ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

በመሆኑም የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ወጤታማ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤክስፕሬስ እና የክልል ኤርፖርቶች ፋሲሊቲና ጥገና አስተባባሪ አቶ ተወልደ ግርማይ፤ መንግስት የሽሬ አየር ማረፊያ በፍጥነት አገልግሎት እንዲሰጥ ያላሰለሰ ጥረት አድረጓል ብለዋል፡፡

በዚህም አውሮፕላን ማረፊያው ተጠግኖ በፍጥነት አገልግሎት መስጠት እንዲችል በከፍተኛ ትኩረት የጥገና ስራዎች ስለመከናወናቸውም አብራርትዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም