በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል በጋራ እንደሚሠሩ የሶስት ክልል ተጎራባች ዞኖች ገለጹ

52

ነገሌ (ኢዜአ) ታህሳስ 24/2015 በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከልና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በጋራ እንደሚሠሩ የኦሮሚያ፣ የደቡብና የሲዳማ ክልሎች ተጎራባች ዞን አመራሮች ገለጹ።

ከኦሮሚያ፣ ከደቡብና ከሲዳማ ክልል የተውጣጡ የአራት ዞን አመራሮች በምእራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ጓንጓ ከተማ ትላንት በአካባቢያዊ የጸጥታ ጉዳይ ላይ መክረዋል፡፡

የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዱላ ሂርባዬ በአዋሳኝ አካባቢ የሚያጋጥም የጸጥታ ችግር ሁሉንም ተጎራባቾች ዞኖች የሚጎዳ ነው ብለዋል።

ሽብርተኛው ሸኔ ባለፉት አመታት ከምዕራብ ጉጂ አልፎ በአዋሳኝ ዞኖችም በንጹሀን ላይ ጥቃት ሲያደርስ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

''የጸጥታ ችግሩን ለመከላከል በጋራ መሥራት በመቻላችን የሽብር ቡድኑ የሀገር ጠላት እንደሆነ ሕዝባችን ተረድቶ ቡድኑን እያጋለጠ ይገኛል'' ብለዋል፡፡

የህግ የበላይነት ተከብሮ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ጸረ ሰላም ሀይሎችን በጋራ መከላከል አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉም አመልክተዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ስለሽ ደነቀ ''የምዕራብ ጉጂ ዞን የጸጥታ ችግር እኛንም ይመለከታል'' ብለዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ከምዕራብ ጉጂ ዞን ጋር በመቀናጀት አሸባሪው ሽኔ ወደ ዞኑ እንዳይገባ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የሽብር ቡድኑን በመደገፍ የተጠረጠሩ ግለሰቦችንም በመያዝ ለምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳደር አሳልፈው መስጠታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የጌዲዮ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አበባየሁ ኢሳያስ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ ወደ ዞኑ ሰርጎ እንዳይገባ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሆኑም አብራርተዋል፡፡

በዞኑ የጸጥታ ሀይሎች በተደረገ የተጠናከረ ጥበቃ አደንዛዥ እጾች፣ ሀሰተኛ የብር ኖቶችና በርካታ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉም አስታውሰዋል፡፡

''በመካከላችን የተፈጠረው መቀራረብ የውስጥ አሰራሮቻችንን ጭምር በጥልቀት ፈትሸን የጸጥታ ስጋቱን ለመቀነስ አግዞናል'' ብለዋል ኃላፊው፡፡

በምክክር መድረኩ የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ የምእራብ ጉጂ፣ የጋሞ ጎፋና የጌድዮ እንዲሁም ከሲዳማ ክልል የሎካ አባያ ዞኖች የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም