በኦሮሚያ ክልል ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የማህበረሰብ ጤና መድህን በትኩረት እየተተገበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የማህበረሰብ ጤና መድህን በትኩረት እየተተገበረ ነው
ታህሳስ 24/2015 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የማህበረሰብ ጤና መድህን ጉልህ ድርሻ ያለው በመሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።
27ኛው የጉሚ በለል የውይይት መድረክ "የማህበረሰብ ጤና መድህን ለማህበረሰቡ ጤና ዋስትና ነው" በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መንግስቱ በቀለ እንዳሉት የጤናው ዘርፍ ዋነኛ ተልእኮ ጤናን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ ነው።
ሰው በአቅም ማነስም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ከጤና አገልግሎት መከልከል እንደሌለበት ያነሱት ሃላፊው ለዚህ ተልእኮ መሳካት ደግሞ የማህበረሰብ ጤና መድህን ዋናው ስልት ነው ብለዋል።
ሁሉም የክልሉ ሕዝብ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የማህበረሰብ ጤና መድህንን በስፋት ለመተግበር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ።
"ለፕሮግራሙ ስኬት በየደረጃው ያለው አመራር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ያሉት ደግሞ በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በክልሉ ጤና ቢሮ የማህበረሰብ ጤና መድህን አስተባባሪ አቶ ዲንቃ ኢረና ናቸው።
የክልሉ የማህበረሰብ ጤና መድህን ሽፋን ወጥነት ባለው መልኩ እየተተገበረ አለመሆኑን ያነሱት አስተባባሪው ከዞን ዞንም ሆነ ከወረዳ ወረዳ ልዩነቱ ሊሰፋ የቻለው በአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ካሉት 338 ወረዳዎች ፕሮግራሙ በ335ቱ ወረዳዎች በመተግበር ላይ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም በክልሉ 20 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎችን የጤና መድህን ፕሮግራም አባል ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በውይይቱ የተገኙት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና መድህን የአባላት ማፍራትና የመዋጮ ማሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ጉደታ አበበ በበኩላቸው የፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ አዋጅ መውጣቱና የማህበረሰብ ጤና መድህን ምክር ቤት መቋቋሙ ዘርፉን የተሻለ ለማንቀሳቀስ ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
በውይይት መድረኩ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች ተገኝተው ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን በዘርፉ ጥሩ አፈጻጸም ያላቸው ዞኖችና ወረዳዎችም ልምዳቸውን አካፍለዋል።