ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን አስደናቂ ባህል፣ ቅርስና ታሪኮች በስፋት በማስተዋወቅ ለጋራ ጥቅም እንዲውሉ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 24/2015 በኢትዮጵያ በብዙ አካባቢዎች ያሉ አስደናቂ ባህል፣ ቅርስና ታሪኮችን በማስተዋወቅ ለአገር ልማትና የጋራ ጥቅም እንዲውሉ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።

የወሎ የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የባህል ጉባዔና ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል።

ከታኅሳስ 19 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም የተካሄደውን ፌስቲቫል የወሎ ዩኒቨርሲቲና ቫይብራኔም ሪሶርስ ፋውንዴሽን በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፤ የአካባቢውን ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ማስተዋወቅ ያስቻለ ሁነት ሆኗል።

የወሎ አጠቃላይ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች እንዲሁም በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ያሉ እምቅ ሃብቶች ለእይታ ቀርበዋል።

ፌስቲቫሉ ላይ ከተገኙት አርቲስቶች መካከል ኢዜአ ያነጋገረው ሙዚቀኛ ደርብ ዘነበ፤ በፌስቲቫሉ ላይ ስለ ወሎ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ማግኘት አስችሎኛል ብሏል።   

"በተለይም በጉብኝቴ የማላውቃቸው አዳዲስ ታሪኮችን አውቄያለሁ" ያለው ሙዚቀኛ ደርብ፤ ስለ ወሎ ታሪክ መጻሕፍቶችን በማንበብ ተጨማሪ እውቀት እንድገበይ የሚያነሳሳ ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ በብዙ አካባቢዎች ያሉ አስደናቂ ባህል፣ ቅርስና ታሪኮችን በማስተዋወቅ ለአገር ልማትና የጋራ ጥቅም እንዲውሉ መሥራት ይገባል ብሏል።

በዚህ ረገድ የወሎ ሕዝብ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶችን የሚያስተዋውቀው ጉባዔና ፌስቲቫል ምሳሌ መሆኑን ጠቅሶ፤ እንዲህ ዓይነት ሁነቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብሏል።

ኢትዮጵያዊነት በጠንካራ መሰረት ላይ የሚቆመው ሕዝቦች እሴቶቻቸውን በጋራ በማጎልበት መጠቀም ሲችሉ መሆኑን ጠቅሷል።

የቫይብራኔም ሪሶርስ ፋውንዴሽን መሥራች ዶክተር መሐመድ ሳኒ፤ የመርሃ-ግብሩ ዓላማ የቀደሙት አያቶች ለትምህርት፣ ለሳይንስና ጥበብ እንዲሁም ለአገር የነበራቸውን ፍቅር እና መስዋዕትነት ለአሁኑ ትውልድ ለማሳወቅና ሰፊ ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።      

እንዲህ ዓይነት ዝግጅቶች በሌሎች አካባቢዎች እንደሚካሄድ ያነሱት ዶክተር መሐመድ ከታኅሳስ 29 እስከ ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም በደሴ ከተማ ተመሳሳይ መርሃ-ግብር ይካሄዳል ብለዋል።

የትምህርት ፌስቲቫል፣ የሂሳብና ፈጠራ ውድድር፣ የፈረስ ግልቢያና ሌሎችም መርሃ-ግብሮች እንደሚኖሩ አስረድተዋል።

የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎችም እንደሚጎበኙም ዶክተር መሐመድ ጠቅሰው በወሎ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ምሁራን የሚሳተፉበት ሲምፖዚየም እንደሚኖርም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም