ለመጪው የገና በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለመጪው የገና በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በቅንጅት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 24/2015 ለመጪው የገና በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ለገና በዓል የምርት አቅርቦትን በተመለከተ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ህብረት ስራ ኮሚሽን፣ የስኳር ኮርፖሬሽን እና የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ፍላጎት ስለሚጨምር የአቅርቦት ክፍተት እንዳይፈጠርና ህብረተሰቡ ላልተገባ ዋጋ እንዳይጋለጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ሲሰራ መቆየቱን ገልጿል፡፡
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ መስከረም ባህሩ አስፈላጊ ቅድመ-ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የግብርና ምርቶች፣ የእንስሳት ውጤቶች እና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እቅርቦት እጥረት እንዳይኖርና ማህበረሰቡ ላልተገባ ዋጋ ጭማሪ እንዳይጋለጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተብራርቷል፡፡
የፌዴራል ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ በበኩላቸው በአዲስ አበባ 137 ሸማች ማህበራት በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ ኤግዚቢሽንና ባዛር ማካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በቅዳሜና እሁድ ገበያ ማዕከላት ምርቶች እየቀረቡ በመሆኑ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት እንዲሸምትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የምርት እጥረት እንደሌለ የገለፁት ምክትል ኮሚሽነሩ ሽንኩርት ከ15-22፣ ቲማቲም ከ15-23፣ ጤፍ 44-49፣ ስንዴ ዱቄት በኪሎ 55፣ በቆሎ ዱቄት 33 እንዲሁም ዶሮ ከ350-500 ብር በህብረት ስራ ኮሚሽን በኩል እየቀረቡ በመሆኑ ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲሸምት ምክትል ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
161 ሺህ 200 ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች ወደ ገበያ መቅረባቸውን የገለፁት አቶ አብዲ ከ225 በላይ የህብረት ስራ ማህበራት ልኳንዳ ቤቶች በዓሉን በማስመልከት በተመጣጣኝ ዋጋ ስጋ እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል የስኳር ኮርፖሬሽን ማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ አቶ ታፈሰ አሰፋ በበኩላቸው በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከ100 ሺህ አስከ 150ሺህ ኩንታል ስኳር በዓሉን ምክንያት በማድረግ በመላ ሀገሪቱ እየተሰራጨ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ30ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር እየተሰራጨ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ቀፀላ ሸዋረጋ በበኩላቸው በሁለት የመንግስት የልማት ድርጅቶች በኩል 43 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ግዥ መፈፀሙንና ከዚህ ውስጥ 5 ሚሊዮን ሊትር እየተጓጓዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለ3 ሊትር ዘይት 314፣ ባለ 5 ሊትር 509፣ እንዲሁም ባለ 20 ሊትር በ2001ብር ለገበያ የቀረበ በመሆኑ ህብረተሰቡ በተረጋጋ ሁኔታ በዓሉን እንዲያሳልፍ ጠይቀዋል፡፡