ምሁራንን የዲፕሎማሲ አቅም አድርጎ መጠቀም ይገባል-ዶክተር አህመዲን መሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
ምሁራንን የዲፕሎማሲ አቅም አድርጎ መጠቀም ይገባል-ዶክተር አህመዲን መሐመድ
ታህሳስ 24/2015 (ኢዜአ) ምሁራንን የሰው ኃይልን ከማልማት ጎን ለጎን የዲፕሎማሲ አቅም አድርጎ መጠቀም ላይ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።
“በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ካውስል አባላት ምክክር መድረክ መጠናቀቁ ተገልጿል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ እና የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አህመዲን መሐመድ በምክክሩ ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ምሁራንን የሰው ኃይል ከማልማት ጎን ለጎን የዲፕሎማሲ አቅም አድርጎ መጠቀም ላይ መስራት ይጠበቅባቸው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ አሊ ከድር በበኩላቸው ዘላቂ ሰላምን ከመገንባትና አገራዊ ምክክሩን ከመደገፍ አንፃር የምሁራን ተሳትፎ በምርምርና ትንተና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የወራቤ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ቶፊቅ ጀማል በማኅበራዊ ዘርፍ የሚደረጉ ምርምሮች በማኅበረሰቡ ውስጥ የተዛነፉ ጉዳዮች ካሉ በማስተካከልና የመረጃ ምንጭ በመሆን ለሀገር ግንባታው የራሳቸውን አስተዋፅኦ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችና የካውንስል አባላቱ የወራቤ ከተማን የማፅዳት ሥራ ማካናወናቸውንና ፅዳቱ ቀጣይ እንደሚኖረው የሥራ ኃላፊዎቹ መናገራቸውን ከዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ከነገ ጀምሮ በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ቴክኒካል ረዳቶችና አስተዳደር ሰራተኞች ለሁለት ቀናት እንደሚወያዩም በመረጃው ተመላክቷል።