ቀጥታ፡

በህገ-ወጥ መንገድ የገቡ 100 ላፕቶፖችና የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ተያዙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታኅሳስ 24/2015 ሕጋዊ እቃዎችን ሽፋን በማድረግ በኮምፒውተር ሞኒተር ውስጥ ተደብቀው የገቡ 100 ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን ገለጸ።

በሞጆ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ህጋዊ እቃዎችን ሽፋን በማድረግ በኮምፒውተር ሞኒተር ውስጥ ተደብቀው የገቡ 100 ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች፣ ሀርድ ዲስኮች እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መያዛቸው ተገልጿል።

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የህግ ተገዥነት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ፈረጃ አታላይ፣ የሞኒተሩን ክፍል ባዶ በማድረግና በምትኩ አዳዲስ ላፕቶፖችን፣ ሃርድ ዲስኮችን እንዲሁም ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በማስገባት እና መልሶ በማሸግ በህገ-ወጥ መንገድ ሊገቡ የነበሩ 100 ላፕቶፖች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

በተገኘው የፍተሻ ውጤት መሰረትም በሰነድ ላይ ያልተገለፀው ዕቃ የቀረጥና ታክስ መጠን ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያለው አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑንና በእቃዎቹ ላይም የውርስ ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ፈረጃ አክለውም፤ የስሪት ሀገርን ማሳሳት፣ ህጋዊ እቃዎችን ሽፋን በማድረግ ህገ-ወጥ እቃዎችን ማስገባት እና ሌሎች የማጭበርበሪያ ስልቶችን በመጠቀም ህገ-ወጥ ስራ የሚሰሩ አንዳንድ አስመጭና ላኪዎች እንዳሉ ጠቁመው በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በሚደረገው ጥብቅ ቁጥጥር እና ፍተሻ ዓላማቸው እንዲከሽፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ባለፉት 5 ወራት የአስመጭዎችን የህግ ተገዥነት ለማረጋገጥ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ እና ክትትል ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ከጉመሩክ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም