በአንደኛ ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና አዲስ አበባ ፖሊስ በወንዶች እና በሴቶች አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በአንደኛ ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና አዲስ አበባ ፖሊስ በወንዶች እና በሴቶች አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 23/2015 አዲስ አበባ ፖሊስ በ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር ብሔራዊ የክለቦች ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ ሆኗል።
ከታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮና ዛሬ ተጠናቋል።
አዲስ አበባ ፖሊስ፣ፌደራል ፖሊስ፣ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ድሬዳዋ ከተማ፣የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ደሴ ከተማ፣ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ ተሳትፈዋል።
በወንዶች ከ48 እስከ ከ92 ኪሎ ግራም በላይ(92 ፕላስ)፤ በሴቶች ከ48 እስከ 63 ኪሎ ግራም ውድድሩ የተካሄደባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።
በሻምፒዮናው መዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ እያሱ ወሰን፣ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፣ብርጋዴር ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ፣ የቀድሞ ቦክሰኞች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በሻምፒዮናው አዲስ አበባ ፖሊስ በወንዶችም በሴቶችም አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል።
ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮናው ለክለቦች የውድድር አማራጭ መፍጠርን አላማ በማድረግ መካሄዱን የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም በሕንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሴቶች የቦክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ለመምረጥ እንደሚያግዝም ነው የተነገረው።
ሻምፒዮና በወንዶች 90 እንዲሁም በሴቶች 30 በድምሩ 120 ተወዳዳሪዎች መሳተፋቸው ተገልጿል።
በሻምፒዮናው አጠቃላይ አሸናፊ ለሆኑት ክለቦች የዋንጫ እንዲሁም ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቷል።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ እያሱ ወሰን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ክለብ የ50 ሺህ ብር ሽልማት አበርክተዋል።
በመዝጊያ ስነ ስርዓቱ በርካታ የቦክስ ስፖርት አፍቃሪያን በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ተገኝተው ጨዋታዎችን ተከታትለዋል።
ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ሻምፒዮና በዓመት አራት ጊዜ እንደሚካሄድ እና ይህም ለክለቦች የውድድር አማራጮችን እንደሚያሰፋ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የዓመቱ ቀሪ ሶስት ውድድሮች በጎንደር፣አርባ ምንጭ እና አዲስ አበባ ከተሞች ለማከናወን መታሰቡን ገልጿል።
በአራቱ ከተሞች የሚካሄዱት ውድድሮች አጠቃላይ ውጤት ተደምሮ በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ ክለቦች እንደሚለዩም ፌዴሬሽን አመልክቷል።
አዲስ አበባ ፖሊስ የ2014 ዓ.ም ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው።