የቱሪዝም መስህቦችን ለይቶ ለጎብኝዎች መረጃን ተደራሽ የሚያደርግ መተግበሪያ ተዘጋጀ

34

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ታህሳስ 23/2015 የኢትዮጵያ ጠፈር ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩትና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በትብብር ባካሄዱት ጥናት የቱሪዝም መስህቦችን ለይቶ መረጃን ለጎብኝዎች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል “ጎ-ትራቭል” የተሰኘ መተግበሪያ ማበልጸጋቸውን አስታወቁ፡፡

በኢትዮጵያ ጠፈር ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩትና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትብብር በደቡብ ክልል በጋሞና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በቱሪዝም ዘርፍ ለአንድ ዓመት በተካሄደ ጥናትና በተከናወኑ ስራዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በጥናት የበለጸገው መተግበሪያ በደቡብ ክልል በጋሞና ደቡብ ኦሞ ዞኖች 358 የቱሪዝም መገኛ ስፍራዎችን በካርታ አስደግፎ መለየትን ጨምሮ የመስህብ ስፍራዎችን መረጃ ለጎብኚዎች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስችልም ተጠቁሟል።

በምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ጠፈር ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርማቲክ ኢንስቲትዩት ሃላፊ ተወካይ ዶክተር ቱሉ በሻ በወቅቱ እንደገለጹት ተቋሙ ከጠፈር ላይ የሚገኙ መረጃዎችን ለግብርና፣ ለከተማ ልማት፣ ለመሠረተ ልማት፣ ለሀይል ማመንጫና ለቱርዝም ዘርፍ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሰራ ነው።

በተጨማሪም ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ መተግበሪያዎችን እያበለጸገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በጥናት የበለጸገው መተግበሪያው ዘርፉን ዘመናዊነት ከማላበስ ባለፈ ጎበኝዎች የሚፈልጉትን የመስህብ ስፍራ በቀላሉ በማግኘት ከአላስፈላጊ የጊዜ ብክነትና ድካም የሚታደጋቸው መሆኑን አመልክተዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሙልጌታ ደበሌ በበኩላቸው ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር በሁለቱ ዞኖች የሚገኙ የቱርስት ስፍራዎችና መሠረተ-ልማቶች በጥናት መለየታቸውን ተናግረዋል።

ጥናቱ በተጨማሪም የመሬት አጠቃቀም ካርታ ስራና ጎብኚዎች መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያግዝ መተግበሪያ የማበልጸግ ስራን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

"መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከለያቸው አምስት የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው" ያሉት ዶክተር ሙልጌታ ፕሮጀክቱ የቱርዝም ኢንዱስትሪና ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ማሳለጫ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሃይለማሪያም አጥናፉ በበኩላቸው የበለጸገው መተግበሪያ ማንኛውም ሰው በየትኛውም ስፍራ ሆኖ ተንቀሳቃሽ ስልክና ላፕቶፕ ኮምፒውተር በመጠቀም መስህቦችና ተያያዥ አገልግሎቶች ያሉበትን አድራሻ በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

መተግበሪያው በቅርቡም በጎግል ፕሌይ ስቶር ላይ በመጫን ለተጠቃሚ ተደራሽ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

በደቡብ ክልል ባህልና ቱርዝም ቢሮ ሃላፊ ተወካይ አቶ እንዳሻው በቀለ በበኩላቸው ደቡብ ክልል በርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሀብቶች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሀብቶቹ ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ ድርሻ አንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የቱሪዝም ሀብቶች መሠረተ-ልማት ካልተሟላላቸው ተገቢውን ጥቅም እንደማይሰጡ ጠቁመው የክልሉ መንግስት የመሠረተ ልማት ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የ10 ዓመት የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም