አትሌት ለተሰንበት ግደይ የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር አሸናፊ ሆነች - ኢዜአ አማርኛ
አትሌት ለተሰንበት ግደይ የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር አሸናፊ ሆነች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 23/2015 የዓለም ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር አሸናፊዋ አትሌት ለተሰንበት ግደይ የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን በድንቅ ብቃት አሸንፋለች።
ውድድሩ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ ለ40ኛ ጊዜ በሱሉልታ ሲካሄድ የዓለም ሻምፒዮኖች፣ የኦሎምፒክ ኮከቦችና ሌሎች ጠንካራ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
የዛሬ ወር በቫሌንሺያ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯን አድርጋ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የቻለችው ለተሰንበት በአስደናቂ ብቃትና በፍፁም በራስ መተማመን የጃንሜዳን አገር አቋራጭ የአዋቂ ሴቶች የ10 ኪ.ሜ ውድድር አሸንፋለች።
ለተሰንበት በአገር አቋራጭ ውድድሮች ከጃንሜዳ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከወጣት እስከ አዋቂ በርካታ ድሎችን ማሸነፍ ችላለች።
ይህም ለተሰንበትን ከረጅም ርቀት የምንጊዜም ኮከቧ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ወዲህ ከመም እስከ ጎዳና ላይ ውድድሮች ከማራቶን እስከ አገር አቋራጭ ውድድሮች ስኬታማ በመሆን በሁሉም ረገድ የተዋጣላት አትሌት አድርጓታል።
ይህች ድንቅ ወጣት አትሌት የጃንሜዳን ውድድር በማሸነፏ በዚህ ዓመት በአውስትራሊያ በሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክላ ለተጨማሪ ዓለም አቀፍ ክብር እንደምትፋለም ኢፕድ ዘግቧል።
ለተሰንበትን ተከትለው ጌጤ አለማየሁ 2ኛ፣ መቅደስ አበበ 3ኛ፣ ፅጌ ገ/ሰላማ 4ኛ፣ ፎቴን ተስፋዬ 5ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
በተመሳሳይ የአዋቂ ወንዶች የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ወጣቱ ኦሊምፒያን በሪሁ አረጋዊ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ ሲሆን፣ ታደሰ ወርቁ፣ ጌታነህ ሞላ፣ ሞገስ ጥኡማይ፣ ጭምዴሳ ደበሌ እና ኃይለማርያም አማረ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘው አጠናቀዋል።
በወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር ለምለም ንብረት ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ መልክናት ውዱ እና ትነብ አስረስ እስከ ሶስት ባለው ደረጃ አጠናቀዋል።
በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር ደግሞ በረከት ዘለቀ፣ ቦኬ ድሪባ እና አቤል በቀለ ቀዳሚዎቹን ደረጃዎች ይዘው ጨርሰዋል።