ኢዜአ የጀመረውን ተቋማዊ ለውጥ በማሳካት በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ እንዲሆን እንሰራለን – ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

33

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 22/2015  ኢዜአ የጀመረውን ተቋማዊ ለውጥ በማሳካት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ትክክለኛ መረጃዎችን በፍጥነት ተደራሽ የማድረግ ተልዕኮውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተገቢው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግለት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አዳዲስ የቦርድ አመራሮች ዛሬ ከኢዜአ አመራሮች ጋር ትውውቅ ያደረጉ ሲሆን የተቋሙን አዲስ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጎብኝተዋል።

በዕለቱ ለቀድሞ የቦርድ አመራሮች የእውቅና እና ምስጋና መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

የኢዜአ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፤ ኢዜአ በልዩነት  ሀገራዊ ተልዕኮ የተሰጠው ትልቅ የዜና ወኪል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዜና እና ዜና ነክ ዘገባዎችን በመሥራትና በማሰራጨት  በሀገር ውስጥና በውጭ ዋነኛ የዜና ምንጭ የመሆን ተልዕኮውን  በአግባቡ ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ከተመሰረተ 80 ዓመታት እድሜን ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፤ አጠቃላይ ተቋማዊ ለውጥ እያደረገ መሆኑን በማንሳት ለውጡ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢዜአ ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ በመንግሥት ልዩ ትኩረትና ድጋፍ  እየተደረገለት ነው ብለዋል።

አዲሱ የሥራ አመራር ቦርድም ተቋሙን በተሰጠው ተልዕኮ ልክ በማገዝ  ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ መረጃዎችን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢዜአ የሥራ አመራር ቦርድ አባልና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው፤ ኢዜአ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚናውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችለው የለውጥ ጎዳና ውስጥ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

በመሆኑም የጀመረውን ሁሉንአቀፍ የለውጥ ሂደት በቴክኖሎጂ ይበልጥ በመደገፍ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ እንሰራለን ነው ያሉት።

ሌላኛው የቦርድ አባል አቶ ሙሳ አህመድ፤ ተቋሙ የያዘውን ግብ ለማሳካት ብቁ የሰው ሀብት ማፍራት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም አሁን ካለበት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አዲሱ የቦርድ አመራር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ወይዘሮ ሚሊዮን ተረፈ በበኩላቸው፤ ኢዜአ ረዥም ዘመናትን በታማኝ የዜና ምንጭነት ለሀገር ሲያገለግል መቆየቱን አስታውሰው፤ አንጋፋው ተቋም አስደናቂ ለውጥና ሽግግር አድርጎ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ከሚያስጠሩ አንጋፋ ተቋማት መካከል የሚጠቀሰውን ኢዜአን ለማገልገል ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ በሚጠበቅበት ልክ እንዲያገለግል እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የቀድሞ የኢዜአ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በበኩላቸው፤ ኢዜአ ተወዳዳሪና ተመራጭ የዜና ምንጭ መሆን የሚያስችለው ወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በዜና አገልግሎት  ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሙ በጉልህ የሚጠቀስ ተቋም እንዲሆን አዲሱ የሥራ አመራር ቦርድ በትልቅ ኃላፊነት ሊሰራ እንደሚገባ ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም