የኢትዮጵያን የአገረ መንግስት ግንባታ የሚያጸኑ ጠንካራ ተቋማትን እና ትውልድን ለመፍጠር የምሁራን ሚና የላቀ ነው

51

ታህሳስ 22 ቀን 2015 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያን የአገረ መንግስት ግንባታ የሚያጸኑ ጠንካራ ተቋማትን እና ትውልድን ለመፍጠር የምሁራን ሚና የላቀ መሆን እንዳለበት የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

“በአገር ግንባታ የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ የምሁራን ምክክር መድረክ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

በዚሁ ወቅት የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የመከላከያ ሚኒስትርና የአምቦ ዩኒቨርስቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አብርሃም በላይ፤ የአገር ግንባታን በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም ምሁራን የሃሳብና የሞራል መሪነት ሚናቸውን በተግባር ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።  

በርካታ ሀገራት የበለፀጉት በምሁራን ሀሳብ አመንጭነትና መሪነት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ምሁራን በውይይቱ መግባባት ላይ በመድረስ ለሀገር ግንባታ በጎ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ስልጡን፣ ሞራላዊና ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ከመገንባት አንጻር ምሁራን ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ይህንንም በቁርጠኝነት ማሳካት ያስፈልጋል ብለዋል።

ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ጠንካራ ተቋማት እና ትውልድ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም የምሁራን ሚና የላቀ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

የበለጸገችና ለሁሉም ዜጋ የምትመች ሀገርን እውን ለማድረግ ምሁራን መስራት እንዳለባቸው አሳስበው ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠርም  ምሁራዊ አበርክቶ ይጠብቃቸዋል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ያሉ አለመግባባት እና ግጭቶች በዘላቂነት እንዲቆሙ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርምር በማካሄድ ሰላምን የማፅናት ሂደቱ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአምቦ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ባይሳ ለታ በበኩላቸው፤ ምሁራን በሀገር ግንባታ ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምሁራን በየዘመኑ ለሀገር አንድነት፣ ለሰላም እና ለልማት ሲያበረክቱ የነበረውን አስተዋጽኦ በተሻለ መልኩ ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ምሁራን እውቀትና እውነትን የሚሹ፣ ለሌሎች የማሳወቅ ጉጉት ያላቸው እና ከወገንተኝነት የጸዱ መሆን እንዳለባቸው በውይይቱ  ተነስቷል።

በምክክር መድረኩ ላይ ምሁራንን ጨምሮ የምዕራብ ሸዋ ዞን የመንግሥት  የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ምክክር ነገም ቀጥሎ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም