መንግሥት ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው

39

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 22/2015 መንግሥት ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ዜጎች ለማዳረስ እየሰራ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

 የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ምክር ቤት ሥራ ማስጀመሪያና የጤና መድህን ትግበራ 10ኛ ዓመት ክብረ-በዓል መርሃ-ግብር አካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት የዜጎች የኑሮና የጤና ሁኔታን ለማሻሻልና ከድህነት ለማውጣት በርካታ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየሰራ ይገኛል።

የሕብረተሰቡን ጤና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተቀረጸው የጤና ፖሊሲ ጥራት ያለውና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የተቃኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ የማኅበረሰብ ጤና መድህን ሥርዓት ተግባራዊ በተደረገባቸው ወረዳዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን በማጠናከር በቀጣይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።  

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ዜጋ በፍትሃዊነት ለማዳረስ የጤና መድህን ሥርዓት ቁልፍ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

የመድህን ሥርዓቱ አባላት ቅድሚያ በሚያዋጡት አነስተኛ መዋጮ ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ያለስጋት የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል።

ባለፉት አሥር ዓመታት አገልግሎቱን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በ894 ወረዳዎች ተግባራዊ በማድረግ 45 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ የተገኙ ውጤቶችን ዘርዝረዋል።

በቀጣይ በመደበኛ ዘርፍ ለተሰማሩና ለጡረተኞች የማህበራዊ ጤና መድህን ለማስጀመር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በጤናው ዘርፍ ፍትሃዊ የሕክምና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ የጤና ተቋማት በየአካባቢው በመገንባታቸው የጤና አገልግሎት ሽፋን ከ90 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፤ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ለሁሉም ለማዳረስ በፋይናንስ በኩል ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙ የከተማ አስተዳደሮችና የክልል አመራሮች የጤና መድህን ሥርዓት የበለጠ ተደራሽ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ዛሬ የተመሰረተው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ብሔራዊ ምክር ቤት አገራዊ መርሃ-ግብሩን በበላይነት የሚመራ ሲሆን የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችን በአባልነት ይዟል።

የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን መደበኛ ባልሆነ ዘርፍ በተሰማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚተገበር ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በ2003 ዓ.ም የተጀመረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም