የወቅቱ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ወላይታ ድቻ የውድድር ዓመቱን በድል ጀመረ

52

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 22/2015 የወቅቱ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ባህር ዳር ከነማን በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል።

የ2015 ዓ.ም ደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በባሌ ሮቤ ከተማ ተጀምሯል።

በሊጉ መክፈቻ ቀን ሶስት ጨዋታዎች ተደርገዋል።

የአምናው የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ባህር ዳር ከነማን 3 ለ 1 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል።

በሌሎች ጨዋታዎች መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ብሔራዊ አልኮልን 3 ለ 0 እንዲሁም ሙገር ሲሚንቶ መቻልን 3 ለ 1 አሸንፈዋል።

አዲስ አበባ ፖሊስ የመጀመሪያ ሳምንት አራፊ ክለብ ነው።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ስሜነህ በሴ(ዶ/ር) ፣ የመደወላቡ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት አህመድ ከሊል(ዶ/ር) ፣ የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በውድድሩ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተዋል።

የ2015 ዓ.ም ደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ የሶስት ሳምንት ጨዋታዎች በባሌ ሮቤ ከተማ እስከ ረቡዕ ታህሳስ 26 2015 ዓ.ም እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ሳምንት መርሐግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ እንደሚካሄድ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ከ2005 ዓ.ም አንስቶ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም