ኮንቴነር በደረቅ ወደቦች በመከማቸቱ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሊሰበሰብ አልቻለም - ኢዜአ አማርኛ
ኮንቴነር በደረቅ ወደቦች በመከማቸቱ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሊሰበሰብ አልቻለም
አዲስ አበባ መስከረም 21/2011 በደረቅ ወደቦች የተከማቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኮንቴነር በሥራው ላይ እክል እንደፈጠረበት የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት ገለፀ። ገቢ እቃ ተጭኖባቸው ወደ አገር ቤት የገቡና በደረቅ ወደቦች የተከማቹት ኮንቴነሮች በጊዜው ባለመነሳታቸው አገሪቱን ጭምር ለተለያዩ ኪሳራዎቸ እየዳረጉ ነው። ኮንቴነሮቹ በሚፈለገው ጊዜ ባለመነሳታቸው ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከቀረጥና ታክስ መሰብሰብ የነበረበት 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ሊሰበሰብ አልቻለም ተብሏል። ችግሩ በሚፈታበት ሁኔታ ላይ የመከረ ውይይት አስመጪዎችንና አምራች ኩባንያዎችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዛሬ ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት እንደገለፀው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙት ሰባት ደረቅ ወደቦች የተከማቸው የኮንቴይነሮች ብዛት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ከሁሉም ወደቦች በትልቅነቱ በሚጠቀሰው ሞጆ ደረቅ ወደብ ብቻ 13 ሺህ 400 ኮንቴይነር ተከማችቶ የሚገኝ መሆኑን በድርጅቱ የጭነትና አስተላላፊነት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ እመቤት ሻውል ገልፀዋል። ክምችቱ በደረቅ ወደቦች ላይ መጨናነቅ ከመፍጠር ባሻገር እቃዎቹን ለብልሽት እየዳረጋቸውና በአግባቡም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እያደረገ መሆኑም ተገልጿል። አስመጪዎቹ ንብረታቸው ወደብ መድረሱን የሚያሳውቅ የፅሁፍ መልዕክት እንዲደርሳቸው ከማድረግ ባለፈ ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ ጭምር እቃዎቹን እንዲያነሱ ግፊት ቢደረግም ምላሽ የሚሰጡት የተወሰኑ በመሆናቸው ችግሩን ማቃለል እንዳልተቻለ ወይዘሮ እመቤት ተናግረዋል። በድርጅቱ በኩል በቂ የኮንቴይነር ማንቀሳቀሻ መሳሪያ አለመኖሩን ጠቅሰው አሁን ላይ ተጨማሪ መሳሪያዎቸን ለመግዛት ሂደት መጀመራቸውን ገልፀዋል። አስመጭዎችና አምራቾች የሚያስገቧቸውን እቃዎች ሙሉ መረጃ በወቅቱ አለማቅረብ፣ ቀረጥና ታክስ ከፍለው የሚያወጡበት ገንዘብ እጥረት እቃዎቹን ለማንሳት ችግር እንደሆኑባቸው ገልፀዋል። የገቢዎችና ጉምሩክ የቴክኖሎጂ አሰራር መቆራረጥ እና የባለሙያዎቹ አዳዲስ እቃዎችን ናሙና የመለየትና የዋጋ ትመና ላይ የሰው ሀይል አቅም ውስንነትን እንደችግር ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡመር ሁሴን እቃዎቹ በወቅቱ ባለመውጣታቸው ከቀረጥና ታክስ መሰብሰብ የነበረበት 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እንዳልተሰበሰበ ገልፀዋል። በገቢዎችና ጉምሩክ እቃዎቹ ወደብ መድረሳቸውን የሚያሳውቁበት የኤሌክትሮኒክ ጉምሩክ አስተዳደር ቴክኖሎጂ መጠቀም ቢጀምሩም አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመቆራረጥ ችግር፣ ጠንካራ ቴክኖሎጂ አለመኖር እና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ቴክኖሎጂዎችን የማጠናከር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። ሁሉንም አሰራር በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ ከሰው ንክኪ በማራቅ ፍጥነትን ማሻሻልና የኪራይ ሰብሳቢነትን መቀነስ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ከተጀመረው የኤሌክትሮኒክ ጉምሩክ አስተዳደር ቴክኖሎጂ በተጨማሪ አስመጭዎችን የሚመለከቱ ተቋማትን የሚያስተሳስር የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመጀመር እየተሰራ ነው ብለዋል። ከሁሉም በላይ ግን ችግሩ ከአመለካከት ጋር የተያየዘ በመሆኑ ለባለስልጣኑ ሰራተኞች ብቻ ሳይሆን ለንግዱ ማህበረሰብ ጭምር ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ወደብ የደረሰ እቃ በ60 ቀናት ውስጥ እንዲነሳ የሚያደርግ ህግ ቢኖርም ቀኑ ከመብዛቱ የተነሳ አስመጪዎች ደረቅ ወደቦችን መጋዘን እያደረጉ ስለሆነ የቀኑን ብዛት ለመቀነስ ይሰራል ብለዋል። ከሚሰበሰበው ገንዘብ በላይ አገልግሎቱን ስለሚያዘገይ አስመጪዎች በፍጥነት በማንሳት አገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ በኢኮኖሚ ማገዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።