በምዕራብ ወለጋ ዞን 23 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዘር መሸፈኑ ተገለጸ

29

ግምቢ፡ ታህሳስ 22/2015 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን 23 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዘር መሸፈኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት እስታወቀ፡፡

በዞኑ በዚህ ዓመት 35 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ አስካሁን በተከናወኑ ስራዎች 23 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑ ተገልጿል።

በጽሕፈት ቤቱ የግብርና ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ ዋቅሹማ አብዲሳ እንደተናገሩት የታቀደውን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

ለዚህም የሚያስፈልጉ ግበዓቶች ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ መሆኑን ገልጸው የአፈር ማዳበሪያና የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶች ተደራሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዘር ከተሸፈነው 23 ሺህ ሔክታር መሬት ውስጥ 8 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታገጠም አስተራረስ ዘዴ የታረሰ መሆኑን አመላክተዋል።

እስካሁን በዘር የተሸፈነው መሬት በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጸው በአጠቃላይ ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ1 ነጥብ 35 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ የጉሊሶ ወረዳ አርሶ አደር የሆኑት ጌታሁን ታፈሰ ያላቸውን ሩብ ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መሸፈናቸውን ተናግረው ጥሩ ምርት ለማግኘት እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል፡፡

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የአይራ ወረዳው አርሶ አደር ግርማ ማርቆስ ናቸው።

አርሶ አደሩ በበጋ መስኖ ስንዴ በዘር የሸፈኑት መሬት ከ4 ዓመት በላይ ምንም ጥቅም ሳይሰጥ የቆየ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ዓመት ለሙከራ በሩብ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ መዝራታቸውን ተናግረዋል።

የባለሙያ ምክርና ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በመዝራታቸው አሁን ላይ ጥሩ ምርት ለማግኘት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም