ለኢትዮጵያ ሁለተኛዋ የሆነችውን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅ አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ሁለተኛዋ የሆነችውን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅ አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 22/2015 ኢትዮጵያ ሁለተኛዋንና የተሻለ ጥራት ያላትን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅ የሚያስችሉ አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ግርማ ደጀኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በአሥር ዓመት ዕቅድ ውስጥ ሦስት ሳተላይቶችን ለማምጠቅ ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
ከእነዚህ ሦስት ሳተላይቶች መካከል የመጀመሪዋን የመሬት ምልከታን /ETRSS-1/ ሳተላይት ወደ ሕዋ በማምጠቅ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሕዋ ላይ ሆና በርካታ መረጃዎች ስትሰጥ መቆየቷንና አሁንም በመስጠት ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
አሁን ደግሞ በምስል ጥራቷ ከመጀመሪያዋ የተሻለች ሆና የበለጠ አገልግሎት እንድትሰጥ የታሰበችውን ሁለተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዋነኝነትም ሳተላይቷን ለማምጠቅ የሚያስችሉ የአዋጭነት ጥናት መከናወኑን ጠቁመው፤ ሳተላይቷን ለማምጠቅ የሚያስችሉ የግብዓት ማሟላትና አስፈላጊው ጥናት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ሳተላይቷ አገሪቱ በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በቱሪዝምና በተለያዩ የመሬት አስተዳደርና መሰል የምታስገኘውን መረጃ ለማጠናከር ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳላት ጠቁመዋል።
በዚህ የዕቅድ ዘመን ይመጥቃሉ ተብለው ከተያዙት ሦስት ሳተላይቶች መካከል ሦስተኛዋ የኮሙኒኬሽን ሳተላይት መሆኑን ገልጸው፤ ሳተላይቱን የማምጠቅ ሥራ በሂደት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የኮሙኒኬሽን ሳተላይት ተመሳሳይ አገልግሎት እያገኙ ካሉ ሴክተሮች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የኮሙኒኬሽን ሳተላይት በጣም ከፍ ያለ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም ያለው አዋጭነት ቀላል ባለመሆኑ የአገሪቱን አቅም ባገናዘበ መልኩ በቀጣይ ቀሪ ዓመታት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ እቅድ መያዙንም አብራርተዋል።
በ2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕዋ የመጠቀችው የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና በአካባቢው ለተከናወነው የመሬት ምንጣሮ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልነበርም አብራርተዋል።
ይህቺው ታሪካዊ ሳተላይት ከሰጠቻቸው አገልግሎቶች በተጨማሪ ኢትዮጵያን ሳተላይት ካላቸው አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያደረገች መሆኑንም ጠቁመዋል።
የመሬት ምልከታ ሳተላይቷ ሥራዋን ስታቆም እሷን ተክተው ሥራ ላይ የሚውሉ የብዝኃ ሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ በእንጦጦ ኦብዞርባቶሪ ማዕከል ላይ መገንባቱንም ተናግረዋል።
መቀበያ ጣቢያው አምስትና ከዚያ በላይ ከሆኑ የሌሎች አገራት ሳተላይቶች መረጃ መቀበል የሚያስችል መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የሳተላይት ማምጠቅ ሳይንሱም ቴክኖሎጂውም አዲስ ስለነበር በውጭ ባለሙያዎች ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በዘርፉ የባለሙያ አቅም በማደጉ ከዚህ በኋላ በሚመጥቁ ሳተላይቶች ላይ ኢትዮጵያዊያን ብቻ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች አገልግሎታቸው ለግብርና፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለቱሪዝምና በተለይ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሊከሰቱ ለሚችሉ የጎርፍ አደጋዎች የቅድመ ማስጠንቀቅ ሥራ ላይ ከፍ ያለ አገልግሎት ይሰጣሉ።
የሳተላይት ማምጠቅ ሥራው ከቻይና የዘርፉ ተቋም ጋር በመተባበር የሚከናወን መሆኑም ተገልጿል።