ቀጥታ፡

መንግስት ውስብስብ ችግሮችን ተቋቁሞ ያመጣውን አገራዊ ውጤቶች ለማስቀጠል ሙሁራን የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠየቀ

ደሴ (ኢዜአ) ታህሳስ 22/2015 መንግስት ውስብስብ ችግሮችን ተቋቁሞ ያመጣውን አገራዊ ውጤቶች ለማስቀጠል ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠየቀ።

"ለብሔራዊ መግባባትና ሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና'' በሚል መሪ ሀሳብ በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

ምክክሩን ያስጀመሩት የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋርደው እንደገለፁት ምሁራን ወቅታዊ የፖለቲካ፣ የሰላም፣ የኢኮኖሚና ሌሎች ሁኔታዎችን ተረድተው የድርሻቸውን እንዲወጡ የተዘጋጀ መድረክ ነው።

ባለፉት አራት ዓመታት በአገሪቷ ውስብስብ ችግሮች ቢገጥሙም መንግስት ባደረገው ጥረት ተጨባጭ ለውጦችና ውጤቶች መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የለውጥና እድገት የማይፈልጉ የፖለቲካ ሀይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ሁከት መፍጠር፣ የኢኮኖሚ አሻጥር በመስራትና ሌሎች ሴራዎች ተሞክሯል ብለዋል።

ሆኖም መንግስት ከሕዝብ ጋር በመሆን በቅርበት በሰራው ስራ ልምድ የተቀመረባቸው ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ውጤቶቹ ዘላቂ እንዲሆኑና የኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላምና ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ምሁራን የጎላ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።

በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ የወደፊት አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡና ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ተብሏል።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታምሬ ዘውዴ በበኩላቸው ምሁራን አገራዊ ጉዳዩን ተገንዝበው በጥናትና ምርምር ጭምር ለሀገር አንድነትና ዘላቂ ሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለዋል።

ዩኒቨርስቲውም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።

በምክክሩ ምሁራን፣ የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን መድረኩ በሁለት ዙር ከታህሳስ 22 እሰከ 27/2015 ድረስ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም