አካዳሚው ስልጠና በሚሰጥባቸው የተወሰኑ ስፖርቶች ላይ አትሌቶች በክለቦች የመታቀፍ ዕድል እያገኙ አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
አካዳሚው ስልጠና በሚሰጥባቸው የተወሰኑ ስፖርቶች ላይ አትሌቶች በክለቦች የመታቀፍ ዕድል እያገኙ አይደለም
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 22/2015 አካዳሚው ስልጠና በሚሰጥባቸው የተወሰኑ ስፖርቶች ላይ አትሌቶች በክለቦች የመታቀፍ እድል እያገኙ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ገለጸ ።
የአካዳሚው የትምህርት፣ የውድድርና ሥልጠና ዳይሬክተር አቶ አብዮት ተስፋዬ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አካዳሚው በ10 የስፖርት ዓይነቶች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
አካዳሚው ስልጠና ከሚሰጥባቸው ስፖርቶች ውስጥ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ውሃ ዋናና ፓራ ኦሊምፒክ ይገኙበታል።
በእነዚህ ሶስት የስፖርት ዓይነቶች ላይ ግን እንደ አገር የተጠናከሩ ክለቦች አለመኖራቸው ነው የገለጹት።
የክለቦች አለመኖር ደግሞ ሰልጣኞች የአካዳሚው ቆይታ ካጠናቀቁ በኋላ በክለብ የመታቀፍ እድል እያገኙ አለመሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ ስፖርቶች የኦሊምፒክ ስፖርቶች ሲሆኑ ከተሰራባቸው ውጤት የሚመጣባቸውም እንደመሆናቸው ተከታታይነት ያለው ስልጠና አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ነገር ግን አሁን ላይ ከአካዳሚው የሚወጡ ስፖርተኞችም ክለብ እያገኙ አለመሆኑ አስታውሰው፤ የአካዳሚውን ስልጠና ካጠናቀቁ በኋላ የአትሌቶችን እጣ ፈንታ አስቸጋሪ እያደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ የስፖርት አይነቶች የኦሊምፒክ ስፖርት መሆናቸውንና ኢትዮጵያም በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ተሳፎ ማድረጓን ተናግረዋል።
በተሳትፎዋም በወርልድ ቴኳንዶ ከአካዳሚው በወጣው ሰለሞን ቱፋ የተመዘገበው ውጤት አበረታች እንደሆነና ከተሰራበት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ታይቷል።
እንዲሁም በቶኪዮ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጣር 2020 ኦሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያ በፓራ ኦሊምፒክ ተሳትፋ የወርቅ ሜዳሊያም ጭምር ማግኘት ተችሏል ብለዋል።
ይህም የሚያሳየው አካዳሚው የሚወጡ ሰልጣኞች በክለብ የመታቀፈና ተከታታይነት ያለው ስልጠና ካገኙ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለአገራቸው ሜዳሊያ ማምጣት የሚችሉ አትሌቶች ማፍራት እንደሚቻል የሚሳይ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ፌደሬሽኖች የተጠናከሩ ክለቦች እንዲኖሩ መስራት እንዳለባቸው ነው ዳይሬክተሩ ያሳሰቡት።
በተለይ አብዛኞቹ ክለቦች በመንግስት ተቋማት የተቋቋሙ እንደመሆናቸው በአስገዳጅ ሁኔታ እንደዚህ አይነት ስፖርቶች ስልጠና የሚሰጡበት አስራር በመዘርጋት እንደ አገር ለስፖርት እድገት የበኩላቸው አስተዋጽኦ ሊያበረከቱ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
በጉዳዩ ላይ የስፖርት ማህበራቱን ፅህፈት ቤት ሃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገውን ጥረት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ማህበራትን በአዲስ አደረጃጀት እንዲዋቀር እያደረገ በመሆኑ ከአካዳሚ የሚወጡ ሰልጣኞችን በምን መልኩ በክለብ መታቀፍ እንዳለባቸው ምላሽ የሚሰጡ የስራ ሃላፊዎችን ማግኘት አልቻልንም።