የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጸጥታ ችግር ምክንያት መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ዜጎች ቤት ገንብቶ አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጸጥታ ችግር ምክንያት መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ዜጎች ቤት ገንብቶ አስረከበ
ጎንደር (ኢዜአ) ታህሳስ 22/2015 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በማእከላዊና ምእራብ ጎንደር ዞኖች በጸጥታ ችግር ምክንያት መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው 280 አባወራዎች መኖሪያ ቤት ገንብቶ ማስረከቡን አስታወቀ፡፡
ማህበሩ በሚሰጠው ሰብአዊ አገልግሎት የህብረተሰቡን ተሳትፎና ድጋፍ ለማሳደግ የሚያስችል መድረክ በጎንደር ከተማ አካሂዷል፡፡
በማህበሩ የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ እንደተናገሩት ማህበሩ 280 መኖሪያ ቤቶች ገንብቶ ያስረከበው ከሶስት ዓመት በፊት ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ነዋሪዎች ነው፡፡
መኖሪያ ቤቶቹን በ23 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ ባለፉት ሶስት ወራት አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ማስረከብ መቻሉን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም የምግብ ማብሰያ፣ ፍራሾችና አልባሳት ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በዞኖቹ በጸጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በመጠለያ ለነበሩ ወገኖች 145 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሰብአዊ ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 6 ወራት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለችግር ለተጋለጡ ወገኖችና ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት 23 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
ማህበሩ የሚሰጣቸውን ሰብአዊ አገልግሎቶች ማጠናከር እንዲቻል ህብረተሰቡ በገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በማእከላዊ ጎንደር ዞን የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ማለደ ማህበሩ በወረዳው በ2010 ዓ.ም ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ቤታቸው ለተቃጠለባቸው አባወራዎች 40 መኖሪያ ቤቶች ገንብቶ ማስረከቡን ተናግረዋል።
ማህበሩ በወረዳው ተፈናቅለው ለነበሩ ከ19 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የአልባሳት፣ የምግብና የቤት ቁሳቁስ በማቅረብ ሰብአዊ ድጋፍ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡
የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ አደጋ መከላከልና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ ዳንኤል ተገኘ በበኩላቸው ማህበሩ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው አባወራዎች 50 ቤቶችን መገንባቱን ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ከማእከላዊ ጎንደር ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የወረዳ አመራሮችና የተቋማት የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡