የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ለማዳረስ የጤና መድህን መርሐግብርን የበለጠ ተደራሽ ማድረግ ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ለማዳረስ የጤና መድህን መርሐግብርን የበለጠ ተደራሽ ማድረግ ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 22/2015 የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ለማዳረስ የጤና መድህን መርሐግብርን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ብሔራዊ ምክር ቤት ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ እና የጤና መድህን ትግበራ 10ኛ ዓመት ክብረ በዓል መርሀ-ግብር እየተካሔደ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስት የዜጎች የኑሮና የጤና ሁኔታን ለማሻሻልና ከድህነት ለማውጣት በርካታ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎት መርሀ ግብር አብዛኛውን አርሶ አደር የሕብረተሰብ ክፍል የሚያቅፍ ወሳኝ የሆነ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የጤና መድህን ስርዓት በሌሎች አገሮች ያለውን ትግበራ በማንሳት በኢትዮጵያም በፍትሀዊነትና ተደራሽነት የበለጸገና አገሩን የሚወድ፣ ተስፋ የሰነቀ ማህበረሰብን ለመገንባት የጤና መድህን አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
ባለፋት አስር አመታት የጤና መድህንን ተግባራዊ በማድረግ ማህበረሰቡ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ የተገኙ ስኬቶች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ ሁሉን አቀፍ የጤና መድህንን ተደራሽ ለማድረግ የበለጠ መረባረብ እንደሚገባ አቶ ደመቀ አሳስበዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጤና መድህን ሽፍን ቁልፍ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
አገልግሎቱ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በ894 ወረዳዎች ተግባራዊ በማድረግ 45 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በመርሐግብሩ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን የጤና መድህን የ10 አመታት ጉዞን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሏል።