የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት መሻሻል የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ቁጥር ይጨምራል -አንድ የጉዞ ወኪል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት መሻሻል የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ቁጥር ይጨምራል -አንድ የጉዞ ወኪል
አዲስ አበባ መስከረም 21/2011 የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት መሻሻል ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥር እንደሚጨምር አንድ የጉዞ ወኪል ገለጸ። በቻይና ምስራቃዊ ግዛት የሚገኝ የጉዞ ወኪል ለሀገሪቱ የዜና አገልግሎት እንደገለጸው በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለዓመታት የቆየው ውጥረት በቅርቡ መፍትሄ ማግኘቱ ኢትዮጵያ ከወትሮ በበለጠ በብዙ ቱሪስቶች እንድትጎበኝ ያደርጋል ብሏል። የድርጅቱ ባለቤት ሚስተር ሀን ጓንሚንግ ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን የአዲግራት ከተማን ከጎበኙ በኋላ ነው ይህንን የተናገሩት። ኤትዮ-ኤርትራ ከሁለት አስርት ዓመታት የባላንጣነት ዘመን መወገዱ ከምስራቅ አፍሪካ፣ ከእስያና ከአሜሪካ ለቢዝነስና ለመዝናናት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥርን በእጅጉ ያሳድገዋል ሲሉ ለቻይና ዜና አገልግሎት ሽንዋ የተናገሩት። በቻይና የሚገኙ ሌሎች የጉዞ ወኪሎች ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሰሩ ለማድረግም ከትግራይ ክልል ቱሪዝም ቢሮና ከኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር መነጋገራቸውንም ጨምረው ገልፀዋል። የአምባሳደር ፕሮሞሽንና ኢቨንት ካምፓኒ ባለቤት አቶ ሀድጉ ወልዳይም በቻይና ምስራቃዊ ግዛት የሚገኘው ይህ የጉዞ ወኪል በትግራይ ክልል ጉብኝት ማድረጉ በኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ምክንያት እንደሚሆንም አስረድተዋል። የግጭት ቀጠና በነበሩ ኢትዮ-ኤርትራ አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎች ቱሪስት የሚስቡ በመሆናቸውና ሁለቱ ሀገራት አሁን ወደ ሰላም በመመለሳቸው የሀገር ጎብኝዎች ቁጥርን ያሳድገዋል ብለዋል። ቱሪስቶች ወደ አካባቢው ሲመጡ የሚያስገኙትን የኢኮኖሚ ጥቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ስራ መጀመሩንም ገልፀዋል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን በበኩላቸው የኢትዮ-ኤርትራ አዋሳኝ አካባቢ ለእንቅስቃሴ ምቹ መሆኑ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረገውን የቢዝነስ ግንኙነትና አንድነት ገፅታ ይቀይረዋል ብለዋል። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መታደስ ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር የምታደርገውን የባህልና የቱሪዝም ግንኙነትንም የበለጠ እንድታሳድግ እንደሚያግዛትም ተናግረዋል።