በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መሪው አርሰናል ከብራይተን ማንችስተር ሲቲ ከኤቨርተን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መሪው አርሰናል ከብራይተን ማንችስተር ሲቲ ከኤቨርተን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው


አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 22/2015 በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት መርሐግብር የሊጉ መሪ አርሰናል ከብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን፤ ማንችስተር ሲቲ ከኤቨርተን የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
በስፔን ላ ሊጋ ሪያል ማድሪድ ሲያሸንፍ ሲቪያ አቻ ወጥቷል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሐግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በ40 ነጥብ ፕሪሚየር ሊጉን የሚመራው አርሰናል ወደ አሜክስ ስታዲየም በማቅናት ከምሽቱ 2 ሰአት ከ30 ከብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን ጋር ይጫወታል።
አርሰናል ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ብቻ አቻ ወጥቷል።
በሊጉ ትልቆቹን ክለቦች በማሸነፍ እና በመፈተን የሚታወቀው ብራይተን ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎቹ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል።

ብራይተን በ2021/22 የውድድር ዓመት ከአርሰናል ጋር ባደረጋቸው ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸንፍ በተቀረው አቻ ወጥቷል።
የ44 ዓመቱ አንቶኒ ቴይለር የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።
ከምሽቱ 12 ሰአት በኢትሃድ ስታዲየም በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንችስተር ሲቲ ከኤቨርተን ጋር ይጫወታል።
የ39 ዓመቱ አንዲ ማድሌይ የጨዋታው የመሐል ሜዳ አለቃ ናቸው።
በሞሊኒው ስታዲየም የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ዎልቨርሀምፕተን ወንድረርስ ከቀኑ 9 ሰአት ከ30 ማንችስተር ዩናይትድን ያስተናግዳል።
በሊጉ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኒውካስትል ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ፣ ቦርንማውዝ ከክሪስታል ፓላስ እና ፉልሃም ከሳውዝሃምፕተን በተመሳሳይ ከምሽቱ 12 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ትናንት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በተካሄዱ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሊቨርፑል ሌይስተር ሲቲን 2 ለ 1 ብሬንትፎርድ ዌስትሃም ዩናይትድን 2 ለ 0 አሸንፈዋል።
በሌላ በኩል በስፔን ላ ሊጋ ትናንት በተደረጉ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ወደ ጆሴ ዞሪያ ስታዲየም ያቀናው ሪያል ማድሪድ ካሪም ቤንዚማ በጨዋታ እና በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራቸው ግቦች ሪያል ቫያዶሊድን 2 ለ 0 አሸንፏል።

በ82ኛው ደቂቃ የሪያል ቫያዶሊዱ አጥቂ ሰርጂዮ ሊዮን በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ነጮቹ ነጥባቸውን ወደ 38 ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነት በጊዜያዊነት ከባርሴሎና ተረክበዋል።
በሌሎች ጨዋታዎች ጌታፌ ሪያል ማዮርካን 2 ለ 0 ሲረታ ሴልታቪጎ ከሲቪያ እንዲሁም ካዲዝ ከአልሜሪያ በተመሳሳይ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።

ዛሬ ባርሴሎና በካምፕ ኑ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ሌላኛውን የከተማ ተቀናቃኝ ክለብ ኢስፓኞልን ያስተናግዳል።
ባርሴሎን ካሸነፈ መሪነቱን ከሪያል ማድሪድ ይረከባል።