ቀጥታ፡

ሉካ ሞድሪች የመሐል ሜዳው የልብ ምት

(በሙሴ መለስ)

የእግር ኳስ ተንታኞች በዓለም እግር ኳስ ውስጥ ከታዩ የምንጊዜም የአማካይ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ይሉታል። የክሮሺያ የምንጊዜውም ምርጥ ተጫዋች የሚል ስያሜም ይሰጡታል።

የእግር ኳስ ተንታኞች፣አሰልጣኞች እና ከሱ ጋር የተሰለፉ ተጫዋቾች አስደናቂ ኳስ የማቀበል አቅሙ እና ከርቀት የሚያስቆጥራቸው ግቦች በተደጋጋሚ ጊዜ አድናቆት ችረውታል።

ኳስን ሲያቀብል እና ሲመታ የሚጠመዝብበት ቴክኒክ እንዲሁም በጫና ውስጥ ያለው መረጋጋት እና ኳስን ሳይነጠቅ የሚያልፍበት መንገድ ድንቅ የአማካይ ተጫዋች የሚል ስያሜን አሰጥቶታል።

የመሐል ሜዳ አስደናቂ ብቃቱ “ምትሐተኛው”፣ ”የመሐል ሜዳው ዳይሬክተር” እና “አዝናኙ የሜዳ ላይ ንጉስ” የሚሉ ቅጽል ስሞችንም አግኝቷል።

እያወራን ያለነው የእግር ኳስ ጉዞው ከዛዳር እስከ ለንደን፣ ከሞስኮ እስከ ዶሃ ከለንደን እስከ ማድሪድ ስላካለለው ዝምተኛው እና ብርቱው የመሐል ሜዳው ቁንጮ ሉካ ሞድሪች ነው።

ሉካ ሞድሪች በክሮሺያ (በቀድሞ አጠራሯ ሶሻሊስት ሪፐብሊክ ኦፍ ክሮሺያ) ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ራቭኒ ኮታሪ ግዛት በምትገኘው ጥንታዊቷ ከተማ ዛዳር እ.አ.አ መስከረም 9 1985 ተወለደ። በወቅቱ የአሁኗ ክሮሺያ በቀድሞ ዩጎዝላቪያ ስር ነበረች።

የክሮሺያዊው አማካይ ተጫዋች የልጅነት እድገት ክሮሺያ ከእ.አ.አ 1991 እስከ 1995 ነጻነቷን ለማግኘት ካደረገችው ጦርነት ጋር የተገጣጠመ ነው።

የክሮሺያ ኃይሎች ከ‘ሶሻሊስት ፌደራል ሪፐብሊክ ኦፍ ዩጎዝላቪያ’ እና ሰርቦች ይቆጣጠሩት ከነበረው ‘ዩጎዝላቭ ፒፕል አርሚ’ ጋር ለአራት ዓመታት ተዋግተዋል።

አያቱ ሉካ እ.አ.አ ታህሳስ ወር 1991 እሱ ከሚኖረበት ሞድሪቺ አካባቢ በቅርበት በምትገኝ ቦታ ላይ በሰርብ ታጣቂዎች ተገደሉ።

ጦርነቱ በተፋፈመበት ወቅት ሞድሪች እና ቤተሰቦቹ የሚኖሩበትን በዛዳር ግዛት ውስጥ ከምትገኘው ሞድሪቺ ከተሰኘው መንደር ሸሽተው ሄዱ። ከሸሹ በኋላ የሚኖሩበት ቤት በእሳት ተቃጠለ።

ሉካ ሞድሪች ስደተኛ ሆነ። እሱ እና ቤተሰቦቹ ለሰባት ዓመታት አንጻራዊ ሰላም በነበረባት የዛዳር ግዛት በምትገኘው ኮሎቫሬ አካባቢ በምትገኝ ሆቴል ለሰባት ዓመት ኖሯል። ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ከሆቴሉ ቀድሞ ወደ ሚኖርበት ስፍራ በመመለስ ሆቴል አይዜድ የሚባል ሆቴል መኖር ጀመረ።

አባቱ ስቲፔ ሞድሪች የክሮሺያን የጦር ኃይል በጥገና ባለሙያነት ተቀላቀሉ። የወታደራዊ መኪኖች እና ቁሳቁሶችን ይጠግኑ ነበር። እናቱ ራዶይካ ሞድሪች የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ይሰሩ ነበር።

በጦርነቱ ወቅት በጥንታዊቷ ከተማ ዛዳር በሺዎች የሚቆጠሩ ቦምቦች ይዘንቡ ነበር። ለሉካ ሞድሪች ከጦርነት ለማምለጥ በወቅቱ የነበረው ብቸኛ አማራጭ እግር ኳስ መጫወት ብቻ ነበር።

ሞድሪች እሱና ቤተሰቦች በጦርነቱ ወቅት ያሳለፉት በጣም ፈታኝ ጊዜ አሁን ላለው ስብዕና መቀረጽ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራል።

ሉካ ሞድሪች እ.አ.አ 1992 በሰባት ዓመቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የስፖርት አካዳሚ ገባ። በስፖርት አካዳሚ ለነበረው ቆይታ ያለውን ወጪ ትንሽ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦቹ እና አክስቱ ሸፍነውለታል።

“ልጅ ሆኜ እግር ኳስን እንድጫወት ያነሳሱኝ ክሮሺያዊው ኮከብ ዝቮንሚር ቦባን እና ጣልያናዊው ኮከብ ፍራቼስኮ ቶቲ ናቸው” ይላል ሉካ ሞድሪች።

MADRID, SPAIN - AUGUST 27: (EXCLUSIVE COVERAGE) Luka Modric the new signing for Real Madrid poses with a club shirt before his official presentation at Santiago Bernabeu stadium on August 27, 2012 in Madrid, Spain. (Photo by Angel Martinez/Real Madrid via Getty Images)

ሞድሪች በቤተሰቦቹ ድጋፍ በኤንኬ ዛርዳር ክለብ እና በተለያዩ የእግር ኳስ ካምፖች ልምምድ ያደርግ እና ስልጠና ይወስድ ነበር።

የክሮሺያ ሀጁክ ስፕሊት ክለብ ሞድሪችን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቶ የነበረ ቢሆንም “ገና ታዳጊ እና ክብደቱ አነስተኛ ነው” በሚል የማስፈረም ፍላጎቱን ትቶታል።

በጣልያን በተካሄደ የወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ሞድሪች ባሳየው ብቃት እ.አ.አ 2001 ማብቂያ ቶሚስላቭ ባሲች ወደ ዳይናሞ ዛግሬብ ክለብ እንደሚያመራ እድሉን አመቻቹለት። ሞድሪች ወደ ዳይናሞ ዛግሬብ አመራ።

ሞድሪች በዳይናሞ ዛግሬብ ወጣት ቡድን የአንድ ዓመት ቆይታ ካደረገ በኋላ እ.አ.አ በ2003 በቦሲኒያ ሄርዞጎቪና ሊግ ለሚጫወተው ዝርንስኪ ሞታር ክለብ በውሰት አመራ።

እ.አ.አ በ2003/04 የውድድር ዓመት ሞድሪች ባሳየው ሁለገብ ብቃት በ18 ዓመቱ የቦሲኒያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ።

ሞድሪች ስለ ቦሲኒያ ፕሪሚየር ሊግ የአካል ብቃት ላይ መሰረት ያደረገ ውድድር ሲናገር “በቦሲኒያ ፕሪሚየር ሊግ የተጫወተ ተጫዋች የትም ሄዶ መጫወት ይችላል” ሲል በወቅቱ አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር።

ዳይናሞ ዛግሬብ ሞድሪች እ.አ.አ 2004/05 የውድድር ዓመት ለሌላኛው የክሮሺያ ክለብ ኢንተር ዛፕሬሲች በውሰት ሰጠው።

ሞድሪች በኢንተር ዛፕሬሲች በነበረው ቆይታ ክለቡን በክሮሺያ የመጀመሪያ ሊግ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ እና በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ እንዲሳተፍ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የክሮሺያ እገር ኳስ ፌዴሬሽን እ.አ.አ በ2004 የአገሪቷ ኮከብ ተጫዋች በሚል ሽልማት አበርክቶለታል።

ሉካ ሞድሪች እ.አ.አ በ2005 ወደ ዳይኖሞ ዛግሬብ ተመለሰ። በክለቡ ለ10 ዓመታት የሚያቆየውን የረጅም ጊዜ ኮንትራት ፈረመ።ሞድሪች በውሉ አማካኝነት ባገኘው ገንዘብ ለቤተሰቡ አፓርታማ ቤት ገዛ።

እ.አ.አ በ2005/06 የውድድር ዓመት በክሮሺያ ሊግ ለዳይናሞ ዛግሬብ 31 ጨዋታዎችን በማድረግ ሰባት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል። የክሮሺያ ሊግ ዋንጫንም አነስቷል።

እ.አ.አ በ2006/07 የውድድር ዓመት ዳይናሞ ዛግሬብ በድጋሚ የሊጉን ዋንጫ አነሳ። ሞድሪች በ30 ጨዋታዎች ስድስት ጎሎችን አገባ፤ 10 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ቻለ። የዓመቱን የሊጉ ኮከብ ተጫዋችነት ሽልማት አገኘ።

ሉካ ሞድሪች ዳይናሞ ዛግሬብን በውድድር ዓመቱ መጨረሻ እንደሚለቅ አሳወቀ።

እ.አ.አ ግንቦት 5 2008 ዳይናሞ ዛግሬብ በማክሲሚር ስታዲየም በክሮሺያ የመጀመሪያ ሊግ ኤችኤንኬ ሪጄካን 6 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ለክለቡ የመጨረሻ ጨዋታውን አደረገ።

ሉካ ሞድሪች በዳይናሞ ዛግሬብ በነበረው የአራት ዓመት ቆይታ 31 ግቦችን ሲያስቆጠር 29 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሏል።

ሞድሪች ክለቡን ለመልቀቅ ከወሰነ በኋላ ባርሴሎና፣አርሰናል እና ቼልሲ ተጫዋቹን ለማስፈረም ፍላጎት አሳዩ።

ይሁን እንጂ ክሮሺያዊው ተጫዋች እ.አ.አ ሚያዚያ 26 2008 ወደ እንግሊዙ ቶተንሃም ሆትስፐር ጋር ለማምራት ተስማማ።

በክረምቱ የዝውውር ወቅት በ16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ዋጋ ወደ ቶተንሃም አቀና። የሁዋንዴ ራሞስ የክረምቱ የመጀመሪያ ፈራሚ ሆነ። በክለቡ የሚያቆየውን የስድስት ዓመት ውል ፈረመ።

እ.አ.አ ነሐሴ 16 2008 በሪቨርሳይድ ስታዲየም ሚድልስቦሮ ቶተንሃም ሆትስፐርን 2 ለ 1 ሲያሸነፍ የመጀመሪያ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታውን አደረገ።

ሉካ ሞድሪች በለንደኑ ክለብ በነበረው የአራት ዓመት ቆይታ 127 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን አድርጎ 13 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 15 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

እ.አ.አ ነሐሴ 27 2012 የስፔኑ ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ ሉካ ሞድሪችን በ30 ሚሊዮን ዩሮ ማስፈረሙን ይፋ አደረገ።

ሞድሪች እ.አ.አ ነሐሴ 29 201 2 ውስጥ በሳንቲያጎ በርናባው ስታዲየም ሪያል ማድሪድ ከባላንጣው ባርሴሎና ጋር ባደረገው የሁለተኛ ዙር የስፔን አሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ላይ በ83ኛው ደቂቃ ጀርመናዊውን ሜሱት ኦዚል ቀይሮ ገባ።

ሪያል ማድሪድ ባርሴሎናን 2 ለ 1 ያሸነፈ ሲሆን በደርሶ መልስ ውጤት 4 ለ 4 በመውጣት ከሜዳው ውጪ ብዙ ጎል ባገባ በሚለው ሕግ የዋንጫው ባለቤት ሆነ።

ሞድሪች የመጀመሪያ ዋንጫውን ለሪያል ማድሪድ ፊርማውን ባኖረ በ36 ሰአት ልዩነት ውስጥ አነሳ። ሉካ ሞድሪች በሪያል ማድሪድ የእስከ አሁኑ የ11 ዓመት ቆይታው 477 ጨዋታዎችን አድርጎ 37 ግቦችን ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

በአስደናቂ ሁኔታ 70 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል። በሪያል ማድሪድ በርካታ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።

ሶስት የስፔን ላ ሊጋ፣ አንድ የስፔን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ፣አራት የስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊዋንጫ፣አምስት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣አራት የአውሮፓ የአሸናፊዎች አሸናፊ እና አራት የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫን በማንሳት ከፍተኛ ስኬትን ማስመዝገብ ችሏል።

በተለይም ሪያል ማድሪድ ከእ.አ.አ 2015 አንስቶ ለሶስት ተከታታይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ሲያነሳ በዚነዲን ዚዳን ስብስብ ውሰጥ ትልቅ የሚበል አስተዋጽኦ ነበረው። ሉካ ሞድሪች እ.አ.አ 2018 የፊፋ ኮከብ ተጫዋች እንዲሁም የባሎን ዶኦር የእግር ኳስ ሽልማትን ማግኘት ችሏል።

በ2022/23 የውድድር ዓመት በሪያል ማድሪድ ማልያ እስከ አሁን ባደረጋቸው 18 ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሏል። ሉካ ሞድሪች የብሔራዊ ቡድን ቆይታውን የጀመረው ለክሮሺያ ከ15፣17፣18፣19 እና 21 ዓመት በታች ቡድኖች በመጫወት ነው።

ሞድሪች ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው እ.አ.አ መጋቢት 1 2006 ክሮሺያ አርጀንቲና 3 ለ 2 ባሸነፈችበት የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ነበር። እ.አ.አ ነሐሴ 16 2006 ክሮሺያ ጣልያንን በወዳጅነት ጨዋታ 2 ለ 0 ስታሸንፍ ለብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ግቡን አስቆጠረ። ሉካ ሞድሪች ጀርመን እ.አ.አ በ2006 ባሰናዳችው 18ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በአሰልጣኝ ዝላትኮ ክራንቻር ጥሪ የደረጎለት በክሮሺያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ተካተተ።

እ.አ.አ ሰኔ 18 2006 ክሮሺያ በምድብ ስድስት ከጃፓን ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ በተለያይችበት ጨዋታ በዓለም ዋንጫው የመጀመሪያ ጨዋታውን አደረገ። ብራዚል እ.አ.አ 2014 ባሰናዳችው 20ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አገር ብራዚል፣ካሜሮን እና ሜክሲኮ ጋር ብትደለድልም ከምድቧ ማለፍ አልቻለቸም። በብራዚል እና ሜክሲኮ በተመሳሳይ 3 ለ 1 ውጤት ስትረታ ካሜሮንን 4 ለ 0 አሸንፋለች። ሉካ ሞድሪች በሶሰቱም ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል።

ሩሲያ ከአራት ዓመት በፊት ባዘጋጀችው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለክሮሺያ ስኬታማ የውድድር ተሳትፎዋ ነበር። ለፍጻሜው ከፈረንሳይ ጋር ተጫውታ 4 ለ 2 ተሸንፋ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ሉካ ሞድሪች ብሔራዊ ቡድኑን በአምበልነት በመምራት በሰባቱም ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል። ሞድሪች እ.አ.አ ሰኔ 16 2018 በምድብ አራት ክሮሺያ ናይጄሪያን 2 ለ 0 ስትረታ በፍጹም ቅጣት ግብ በማስቆጠር በውድድሩ ታሪክ የመጀመሪያ ግቡን ከመረብ ላይ ማሳረፍ ቻለ።

በዛው ምድብ ክሮሺያ አርጀንቲናን 3 ለ 0 ባሸነፍበት ጨዋታ በ80ኛው ደቂቃ ሉካ ሞድሪች ከ23 ሜትር ርቀት ላይ አክርሮ በመምታት አስደናቂ ግብ ማስቆጠር ቻለ።

ሞድሪች በ21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። የዓለም ዋንጫው ኮከብ ተጫዋች ሆኖም ተመርጧል።

ኳታር ከሕዳር 11 እስከ ታህሳስ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ባሰናዳችው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሞድሪች አገሩ ክሮሺያ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በዓለም ዋንጫው ያሳየው አስደናቂ ብቃት እና ብርታት ከበርካቶች አድናቆት እና ሙገሳ አሰችሮታል። ክሮሺያ በዓለም ዋንጫው ባደረጋቻቸው ሰባቱም ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችሏል። አንድ ቢጫ ካርድ ተመለክቷል። ሉካ ሞድሪች በአራት የዓለም ዋንጫዎች 17 ጨዋታዎቸን በማድረግ ሁለት ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። በዓለም ዋንጫው ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች በ14ቱ አገሩን በአምበልነት መርቷል።

ሉካ ሞድሪች ክሮሺያ በዓለም ዋንጫው የደረጃ ጨዋታ ሞሮኮን 2 ለ 1 ካሸነፈች በኋላ በሰጠው አስተያየት ከብሔራዊ ቡድኑ ራሱን የማግለል ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል። “ የሞሮኮው ጨዋታ ምናልባት በክሮሺያ ማልያ ያደረኩት የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ሊሆን ይችላል። ሕልሜ የዓለም ዋንጫን ማንሳት ነበር ያ አልሆነም። ይሁንና ሁለት የዓለም ዋንጫ ሜዳሊያዎችን ማግኘት ትልቅ ክብር ነው። በክሮሺያ ብሔራዊ ቡድን ባለኝ ቆይታ በጣም ደስተኛ ነኝ። እስከ አውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ውድድር ያለውን ነገር አይቼ በቆይታዬ ዙሪያ ያለወን ነገር አያለሁ” ሞድሪች ለስፔኑ ጎል ሙንዲያል ቲቪ በሰጠው አስተያያት ገልጿል። ሞድሪች ከደረጃው ጨዋታ በኋላ ከአባቱ ስቲፔ ሞድሪች ጋር በመተቃቀፍ እና በማልቀስ ደስታውን የገለጸበት መንገድ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ሉካ ሞድሪች ለክሮሺያ ብሔራዊ ቡድን 162 ጨዋታዎቸን አድርጎ 23 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። አይደክሜው እና የቴክኒክ ተሰጥኦ ባለቤት ሉካ ሞድሪች በ37 ዓመቱ በእግር ኳስ ሜዳ የመሐል ክፍል ቦታ ላይ በአስደናቂ የፈጠራ አቅሙ የጨዋታ ሙቀትን ከፍና ዝቅ ማድረጉን ቀጥሎበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም