የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎችን ለማንሳትና መልሶ ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው

21

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 21/2015 የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎችን ለማንሳትና መልሶ ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አስታወቁ።

"የዜጎች ለጎዳና ሕይወት ተጋላጭነትና የባለድርሻ አካላት ምላሽ" በሚል መሪ ኃሳብ ከፖሊሲ አውጪዎች፤ አስፈፃሚዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ምክክር ተካሂዷል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የጎዳና ተዳዳሪነትን ለመቀነስ መንግሥት ከተለያዩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ጋር እየሠራ ነው።

ከዚህ ቀደም በ11 ከተሞች 22 ሺህ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ማንሳት መቻሉን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በቀጣይም በተለያዩ ከተሞች የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ለማከናወን መታቀዱን አስረድተዋል።

ሚኒስቴሩ ይህንን ግብ ለማሳካት ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ባለፉት ዓመታት በርካታ ዜጎችን ከጎዳና ሕይወት በማንሳት የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመደገፍ የሚረዳ የ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፍ ከኤስ.ኦ.ኤስ የሕጻናት መንደር ከተሰኘው የረድኤት ድርጅት መገኘቱን ገልጸው ዜጎቹን ከጎዳና ለማንሳት የሚሰሩትን ሥራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የኤስ.ኦ.ኤስ ሕጻናት መንደር ኢንተርናሽናል የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ተጠሪ ወይዘሮ ሠናይት ገብረ-እግዚአብሔር በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ችግሩን ለመፍታት ተቀናጅቶና ተናቦ መሥራት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎችን ለመደገፍ በተቋማቸው የአምስት ዓመት ፕሮጀክት መንደፉን አስረድተው፤ ፕሮጀክቱ በከፍተኛ ችግር ጎዳና ላይ የወጡ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም