ቀጥታ፡

በገናና ጥምቀት በዓላት ላይ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 21/2015 በገናና ጥምቀት በዓላት ላይ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ዛሬ በሰጡት መግለጫ መጪዎቹ የገና እና ጥምቀት በዓላት ግብይት ጤናማ እንዲሆን ግብረ-ኃይል አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ግብረ ሀይሉ አቅርቦትን የማመቻቸት፣ እንዲሁም ህገ-ወጥነትና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

በበዓሉ የምግብ ፍጆታዎች፣ የግብርና ምርቶች እንዲሁም ለእርድ የሚውሉ የቁም እንስሳት እጥረት እንዳይኖር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ለዓላቱ የሚያስፈልጉ ዶሮዎች፣ እንቁላልና የእርድ ከብቶች በበቂ ሁኔታ ወደ ከተማዋ እንደሚገቡ ነው የገለጹት፡፡

በተጨማሪም ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

በስኳር ኮርፖሬሽን አማካኝነት 30 ሺህ ኩንታል ስኳር ለተጠቃሚዎች እንደሚከፋፈልም ኃላፊው ጠቁመዋል።

ህገወጥነትን ለመከላከል ጠንካራ የቁጥጥር ስርአት መዘርጋቱን የገለጹት ሀላፊው በዚህም የምርት እጥረት እና ጥራት የሌላቸው ምርቶች ወደ ገበያ እንዳይገቡ ይሰራል ብለዋል።

ፖሊስ፣ የደንብ ማስከበር እና የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን የፍተሻ እና የቁጥጥር ስራዎች እንደሚሰሩም እንዲሁ።

በበአላቱ የምርት እጥረት እንዳይከሰት ቢሮው ከሸማች ህብረት ስራ ማህበራት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ የሚጨምሩ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም