ቀጥታ፡

የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናን በ2 ወራት ውስጥ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት ተደርጓል

ድሬዳዋ (ኢዜአ)ታህሳስ 21/2015 የድሬዳዋን ነፃ የንግድ ቀጠና በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ።

ነጻ የንግድ ቀጠናው የኢትዮጵያንና የአካባቢውን ንግድና ምጣኔ ሃብት ከማሳደግ ባሻገር እስከ 100 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።

የአፍሪካ ቀንድን የንግድና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው የሚጠበቀውና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነፃ የድሬዳዋ የንግድ ቀጠና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከወራት በፊት ተመርቆ ለሥራ ክፍት መደረጉ ይታወሳል።

የነፃ የንግድ ቀጠናው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሚል ኢብራሂም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ቀጠናው የሚጠበቅበትን ተልዕኮ ከዳር ለማድረስ በፌደራል መንግስትና በድሬዳዋ አስተዳደር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ ነው።

"ድሬዳዋ ለቀጣናውና ለዓለም የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች መተላለፊያ ለሆነው የመካከለኛ ምስራቅ ያላት ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ የሚፈለገውን ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው" ብለዋል።

ቀጠናው የተሳለጠ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የደረቅ ወደብ፣ የዘመናዊ ባቡር፣ የየብስና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲሁም የጉምሩክ፣ የመኝታ፣ የኢንሹራንስ፣ የባንኮች እንዲሁም የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው ሆቴል፣ መዝናኛ፣ ንግድን የሚያቀላጥፉ መጋዘኖች፣ አፓርታማዎችና ሌሎች አገልግሎቶችን በባለሃብቱ እንዲገነባ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አቶ ካሚል ገልጸዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ነፃ የንግድ ቀጠናው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱን በሙሉ አቅሙ እንዲጀምር የዝግጅት ሥራው ተጠናቋል።

"ቀጠናው በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀመር በቀን 100ሺህ የሚገመቱ የንግድ አንቀሳቃሾች ድሬዳዋ ገብተው ስለሚወጡ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ ያድጋሉ" ሲሉ አመልክተው ቀጠናው ከ70 እስከ 100 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ቢሮ የጉምሩክ የንግድ ሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ አሊ ካሳው ኮሚሽኑ በነፃ የንግድ ቀጠናው ለሚገቡና ለሚወጡ የንግድ ቁሶች አስፈላጊውን የግብአት ዝግጅትና በቂ የሰው ኃይል በማሟላት የዝግጅት ሥራው አጠናቋል ብለዋል።

የትኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ስኬታማ የሚሆነው አስተማማኝ ሰላም ሲሰፍን በመሆኑ ሰላምን የማረጋገጡ ጉዳይ ተገቢ ትኩረት እንደተሰጠው የገለጹት ደግሞ የቀጠናው የጸጥታ ሀላፊ ኮማንደር መከተ ማሞ ናቸው።

ቀጠናው የኢንዱስትሪ ፓርክ በነበረበት ወቅት ሥራ የጀመሩ ባለሀብቶች በበኩላቸው ቀጠናው ይዞት የሚመጣው በረከት ለነሱም ሆነ ለሀገር ከፍተኛ እድገት ያስገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናው የባንክና የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን ለመስጠት ዝግጅታቸውን ካጠናቀቁት መካክል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንዱ ነው።

የባንኩ የቀጠናው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያሬድ ሙሉጌታ "በቀጠናው ቀልጣፋ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት በማድረግ ባለሃብቶችን እየተጠባበቅን ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም