ቀጥታ፡

የተራቆተ ማሳውን ወደ ደን፤ ደኑንም ወደ ንብ እርባታ የለወጠው ስኬታማ ወጣት

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ታህሳስ 21/2015 የተራቆተ ማሳውን ወደ ደን፤ ደኑንም ወደ ንብ እርባታ የለወጠው ስኬታማ ወጣት

በልሁ ማናዬ በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ ደጋማዋ ደብረ ሲና ከተማ ዙሪያ ቀበሌ የሚኖር ወጣት ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ እስከ 12ኛ ክፍል እንደተማረ የሚናገረው በልሁ፤ ኮሌጅ ገብቶ ትምህርቱን ለመቀጠል በወቅቱ ሁኔታዎች እንዳልተመቻቹለት ያወሳል።

ከዚያም ቤተሰቦቹ ወደ ሚኖሩበት ደብረ ሲና ከተማ በማቅናት በአካባበው በሚገኘው የቤተሰቦቹ ማሳ ላይ ሰብል ማልማት ጀመረ፤ ነገር ግን ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡

በመሆኑም የተራቆተ ማሳውን በደን በመሸፈን ንብ ለማነብ፤ ጊዜ ሳይወስድበትም ማሳውን በደን መሸፈን ጀመረ፡፡

በዚህም ንብ የማነብ ውጥኑን ዕውን አደረገ።

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የጀመረው ባህላዊ ንብ ማነብ ስራ ዛሬ ላይ ከባህላዊ ቀፎ ተጨማሪ በርካታ ዘመናዊና የሽግግር ቀፎዎች ላይ ንብ በማነብ ሌማቱን ከማሟላት ባለፈ የቤተሰቡን ኑሮ እንዳሻሻለ ይናገራል።

"ንብ ማነብ እንደ ንብ ታታሪ መሆን ይጠይቃል" የሚለው በልሁ፤ ንብ የማነብ ስራውን በፍቅርና በትጋት እየሰራ በማር ምርት ስኬታማ ሆኛለሁ ይላል።

ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ብቻ ወደ 80 ኪሎ ግራም የሚጠጋ ማር ለገበያ እንዳቀረበ ገልጾ፤ አሜሪካን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጭምር የእርሱ የማር ደንበኞች እንደሆኑ ይናገራል፡፡

አሁን ላይ የማር ተጠቃሚ ደንበኞቹና እርሱ የሚያቀርበው የማር መጠን እንዳልተጣጣመ የሚናገረው ወጣት በልሁ፤ ከዚህ አኳያ የንብ ማነብ ስራውን በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጿል።

ወጣቶች ንብ ማነብን ጨምሮ በእንስሳት እና በእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ላይ በስፋት ቢሰማሩ የሌማት ቱሩፋት መርሃ-ግብር በቀላሉ እንደሚሳካ 'እኔ ምስክር ነኝ' ይላል።

በተለይም በየአካባቢው ያሉ የደን ሀብቶችን ስነ ምህዳራቸውን በጠበቀ መልኩ ንብ በማነብ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እና ትልቅ አገራዊ አቅም መፍጠር እንደሚቻል ይናገራል፡፡

በዚህም ወጣቶች ከትንሽ ስራ ተነስተው ስራን ባለመናቅ ዕምቅ ጸጋዎችን ወደ በረከት መለወጥ እንደሚገባቸው ይመክራል።

በጣርማ በር ወረዳ የንብ እርባታ ባለሙያው አቶ ዘላለም ደምስ፤ ወረዳቸው በዞኑ በማር ሀብቱ ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸው፤ አንድ ግለሰብ እስከ 50 ቀፎዎች እንዳሉት ገልጸዋል።

ከሶስት ሺህ በላይ ባህላዊ እና ከ800 በላይ ዘመናዊና ሽግግር ቀፎዎች ያለው ጣርማ በር ወረዳ፤ ወጣቶች በቡድን በመሆን በንብ ማነብ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም "ወፍ ዋሻ" የሚሰኝ 16 ሺህ ሄክታር ደንን ጨምሮ በወረዳው ያሉ ተፈጥሯዊ ደኖችንም ወደ ንብ እርባታ በመለወጥ ጣርማበርን የንብ ማዕከል የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ነው የተናገሩት።

ከንብ ማነብ ፈተናዎች አንዱ የግብርና ኬሚካል አጠቃቅም እንደሆነ ገልጸው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን የግብርና ኬሚካል አጠቃቀም ደንብና መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም