ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በአህጉሪቱ ከተከናወኑ ተግባራት በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው-የደን ልማት ተመራማሪዎች

ታኅሳስ 21/2015(ኢዜአ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቋቋም ረገድ በአህጉሪቱ ከተከናወኑ ተግባራት በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የደን ልማት ተመራማሪዎች ገለጹ።

በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን ከሚያሰጓት ተፈጥሯዊ አደጋዎች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

የበለጸጉ አገራት የሚለቁት በካይ ጋዝ ደግሞ ለአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ተጠቃሽ ምክንያት ቢሆንም የችግሩ ዳፋ ግን በካይ ጋዝ በመልቀቅ ረገድ እዚህ ግባ የማይባል አበርክቶ ባላት አፍሪካ ላይ በርትቷል፡፡

በአፍሪካ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ ደግሞ በዚህ ረገድ በአብነት ይጠቀሳል፡፡

በመሆኑም የአፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ በመቋቋም ረገድ የበለጸጉ አገራትን ድጋፍ ሳይጠብቁ የራሳቸውን የቤት ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን በማሳደግ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰተውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቋቋም አጋዥ እየሆነ መጥቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለምታከናውናቸው የቀጣይ ስራዎች ተሞክሮ የሚሰጥ ነው፡፡

በተለይ መርሃ ግብሩ ሀገር በቀል ዛፎች ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑ ደግሞ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደን ልማት ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆኑት ዶክተር ተሾመ ታምራት የአፍሪካ ሀገራት መርሃ ግብሩን ወስደው መተግበር ከቻሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመቋቋም ረገድ የተሻለ ውጤት እንደሚመዘገብ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቦና ኢዲሳ በበኩላቸው፤በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተጀመረው ጥረት ጠቀሜታው ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

መርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ ተራሮችን በደን በመሸፈን በቂ የውሃ ሃብት እና የደን ሃብት እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው ከኢትዮጵያ በሚፈሰው ውሃ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሆኑ ሀገራት እንዳይጎዱም ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የጥምር ግብርና ዴስክ ሀላፊ ብስራት ጌታቸው በበኩላቸው፤በአረንጓዴ ልማት የሚከናወነው ትልቅ ስራ ለአፍሪካ ትልቅ ተሞክሮ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ መልኩ በመርሐግብሩ በተቀናጀ መልኩ ሰፊ የሰው ኃይል በማንቀሳቀስ የልማት ስራዎችን በቀላሉ እውን ማድረግ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት መርሃ ግብሩን ወደ ጎረቤት አገራት ለማስፋት የሄደችበት ርቀት በአህጉሪቱ ያለውን ትብብር በማጠናከር ረገድ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ20 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው ይታወቃል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም