ቀጥታ፡

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና ፌደራል ፖሊስ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

ታኅሳስ 21/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ኢንጅነር) ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን አቅም አቀናጅቶ ለመስራት እንደሚያግዛቸው ገልፀዋል።
በቴክኖሎጂ አቅርቦትና ተጠቃሚነት እንዲሁም በሰው ኃይል ልማት በኩል ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ለሃገር የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እንደሚያስችል አመላክተዋል።

ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ተቀራርቦ በመስራት ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠናም የደህንነት ስጋትን ለመቀነስ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ሚና ወሳኝ መሆኑን ኮሚሽነር ጀነራሉ መግለጻቸውን ከኢንሲቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም