ቀጥታ፡

በጎጆ ኢንዱስትሪ የሚመረቱ እደ ጥበብ ውጤቶች የተሻለ ገበያ እንዲያገኙ እንደሚሰራ ተገለጸ

አዳማ (ኢዜአ) ታህሳስ 21/2015 የጎጆ ኢንዱስትሪን ከማስፋፋት ጎን ለጎን በኢንዱስትሪው የሚመረቱ እደ ጥበብ ውጤቶች በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ይሰራል ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባኤ ሰዓዳ አብዱረሃማን ገለፁ።

በአዳማ ከተማ የመጀመሪያ የሆነው የጎጆ ኢንዱስትሪ እንተርፕራይዝ ማዕከል ተመርቆ በይፋ ስራ ጀምሯል።

የጎጆ ኢንዱስትሪ ማዕከሉን ስራ ያሰጀመሩት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረሃማን እንደገለጹት አዳማ ከተማ ሰፊ የስራ አማራጮችና እድሎች ያሉባት ከመሆኑም ባለፈ የገበያ ትስስሩ ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋና አካባቢዋ ያሉ እምቅ የስራ አማራጮችን በመለየት ወጣቶችን ወደ ስራ በማስገባት ረገድ መስተዳደሩ እያከናወነ ያለው ተግባር ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

የጎጆ እንዲስትሪ ልማት ማዕከል በእደ ጥበብና በፈጠራ ችሎታ ብቁ የሆኑ ወጣቶችና ሴቶች ሙያቸውን ወደ ገቢ እንዲለውጡ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና አለው ነው ያሉት።

በዚህም በርካታ ወጣቶች ራሳቸውን ከመጥቀም አልፈው ለሌሎች ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ ጠቅሰው በአዳማ የተጀመረው የጎጆ እንዲስትሪ በሌሎች የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ እንደገለጹት መስተዳድሩ የከተማዋን ነዋሪ ኑሮ ለማሻሻልና የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ በመደበኛነት ከሚፈጠሩ የስራ እድሎች ባሻገር የጎጆ እንዲስትሪን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ስራ በጀመረው የጎጆ እንዲስትሪ እንተርፕራይዝ ማዕከል 200 የሚሆኑ በእደ ጥበብና በፈጠራ ችሎታ ብቁ የሆኑ ወጣቶችና ሴቶች ሙያቸውን ወደ ገበያ መለወጥ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

በዚህም አሁን ስራ የጀመረው የጎጆ እንዲስትሪ በከተማዋ ልዩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸውንና የእደ ጥበበ ሰራዎችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ለገበያ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ነው ብለዋል።

በተለይ በአልባሳት፣ በጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የተለያዩ የማኑፋክቸሪግን ምርቶች በከተማዋ ተመርቶ ለገበያ እንዲያቀርቡ በማለም መሆኑንም አክለዋል።

በዚህም ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ አልባሳትን ጨምሮ ሌሎች የእንዱስትሪ ምርቶች ለገበያ እንዲያቀርቡ  ከማስቻሉም ባለፈ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ጭምር አጋዥ መሆኑን አመልክተዋል።

''አሁን በአንድ ማዕከል ላይ የተጀመረውን የጎጆ እንዱስትሪ እንተርፕራይዝ ወደ አምስት ለማሳደግ ግብ አስቀምጠን እየሰራን ነው'' ያሉት ከንቲባው በዚህም የከተማዋ ባለሃብቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የአዳማ ከተማ የስራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ለገሰ ተሊላ በበኩላቸው መስተዳደሩ ባለፉት አምስት ወራት 105 ሚሊዮን ብር የብድር አቅርቦትና የሊዝ ማሽን በመግዛት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ማስረከቡን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የመስሪያና መሸጫ ቦታ አቅርቦት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለጎጆ እንዱስትሪ ማስፋፊያ የሚሆኑ ሼዶች የእድ ጥበብና የፈጠራ ችሎታ ላለቸው ወጣቶችና ኢንተርፕራይዞች ተላልፏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም