ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ታህሳስ 21/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር አስታወቀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የዲጂታል አቅም ሲባል የዲጂታል እውቀትና ክህሎት ሲኖር መሆኑን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ይህንን አቅም ለማሳደግ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የሚል ስትራቴጂ ቀርጻ ወደ ሥራ መግባቷን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በግንባር ቀደምትነት ለመምራት የሚችሉ አራት ዘርፎችን ተለይቷል ብለዋል።እነዚህም ግብርና፣ የማምረቻ ዘርፍ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና የቱሪዝም ዘርፎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ስትራቴጂው ከአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና የአስር ዓመት የልማት እቅድ ጋር የተሳሰረ መሆኑንም አስረድተዋል።

ስትራቴጂው ከዓላማዎቹ አንዱ አካታች የሆነ ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ለማሳካት አሰራሮችን የመዘርጋት እንዲሁም የዲጂታል አቅምን ሊፈጥሩ የሚችሉ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ስትራቴጂው በተለይም ሴቶች የዲጂታል እውቀታቸውንና አቅማቸውን እንዲያሳዩ በሚያስችል መልኩ እየተተገበረ መሆኑን አመላክተዋል።

እንዲሁም ከዚህ ቀደም በሴቶች አካታችነት ላይ የነበሩ ክፍተቶችን የመሙላትና የማረም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ሴቶችን በዘርፉ ያላቸውን አሰተዋጽኦ ለማሳደግና ተሳትፏቸውን ለማጠናከር የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የቴከኖሎጂ መሰረተ ልማቶችና ስትራቴጂዎች የሴቶችን የመክፈል አቅም እንዲሁም ተደራሽነት እንዲያረጋግጡ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሴቶች በቴክኖሎጂ አቅማቸውን የሚገነቡበት ትልቅ የኦንላይን ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመንግሥት ተቋማት የሚሰሩ ሴቶች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማሳደግ ራሳቸውን ብሎም ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም