በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሁለተኛው ዙር ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሁለተኛው ዙር ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 21/2015 በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሁለተኛው ዙር ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም በሰጡት መግለጫ በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች በመጀመሪያው ዙር የታቀደውን ሰብዓዊ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በመጀመሪያው ዙር ድጋፍ 141 ሺህ 671 ሜትሪክ ቶን ምግብ ወደ ሦስቱም ክልሎች ተጓጉዟል ነው ያሉት።
በሁለተኛው ዙር ደግሞ እስካሁን ወደ አማራ ክልል 25 ሺህ ሜትሪክ ቶን፣ ወደ አፋር ክልል 2 ሺህ ሜትሪክ ቶንና ወደ ትግራይ ክልል ደግሞ ከ1 ሺህ ሜትርክ ቶን በላይ እህል ተጓጉዟል ብለዋል።
ይህም በሁለተኛው ዙር ድጋፍ ለማድረግ ከታቀደው 20 በመቶ መሆኑን ጠቁመው ቀሪውን ድጋፍ ለማድረግ የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
ድጋፎቹ በአራት ኮሪደሮች እየቀረበ መሆኑንም አብራርተው መልሶ ማቋቋሙን በተመለከተም የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።