ፔሌ - የእግር ኳስ ዕንቁ - ኢዜአ አማርኛ
ፔሌ - የእግር ኳስ ዕንቁ
ስለ ፔሌ ብዙዎች ብዙ ብለዋል፤ ብዙ ሲሰራ ያዩ ያሉትን ቢሉ የሚደንቅ አይሆንም። በእግር ኳሱ አለም ድንቅ ዘመናትን ስላሳለፈው ፔሌ የተረዱትን ከተናገሩት መካከል ፦
ብራዚላዊው ኮከብ ኔይማር “እሱ ቢሄድም የሱ ምትሐቶች ከኛ ጋራ ይኖራሉ” ሲለው ሕንዳዊው ፖለቲከኛ ራሁል ጋንዲ ደግሞ “እግር ኳስ አምባሳደሯን አጥታለች” በማለት ገልጸውታል
የእግር ኳስ ተንታኞች እና አፍቃሪያን “ጥቁር እንቁ” ፣ ‘የእግር ኳሱ ንጉስ’ ፣ “የምንግዜም ብራዚላዊ የእግር ኳስ ኮከብ” እና “የጎል ማሽን” ይሉታል።
በእግር ኳስ መዝናናት ከፈለግክ እና የእግር ካስ ምትሐቶችን ማየት ካሻህ እሱ ሲጫወት ተመልከት ይላሉ በሱ የጨዋታ ጊዜ የነበሩ የእግር ኳስ ተንታኞች።
“የ20ኛው ክፍለ ዘመን ስኬታማ እና ታዋቂው ስፖርተኛ” የሚል ስያሜምው ይሰጡታል።
ከእግር ኳስ ውጪ ባለው የግል ሕይወቱ ያለው መልካም ስብዕና በፍቅር እንድትወደው ያደርገሃል ይላሉ በቅርበት የሚያውቁት ሰዎች።
ብራዚላውያን በእግር ኳስ ጥበቡ ለብራዚል አንድነትን የፈጠረ በማለት ያሞካሹታል።
የእግር ኳሱ ፈርጥ ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሚንቶ ብዙዎች በሚያውቁት ቅጽል ስሙ ፔሌ ትናንት ለሞት እጁን ሰጠ።
በብራዚል ሳኦ ፖሎ በሚገኘው አልበርት አንስታይን ሆስፒታል ሕክምናውን ሲከታተል የነበረው ታዋቂው እና ዝነኛው ተጫዋች ፔሌ በአንጀንት ካንሰር ምክንያት በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
“የንጉሴ ፔሌ የሕይወት ጉዞ አይበገሬነት እና ፍቅር መገለጫው ሆኖ አልፏል” የሚል መልዕክት በተጫዋቹ ይፋዊ የኢንስታግራም ገጽ ላይ ሰፍሯል።
“እቺንም ዓለም በሰላም ተሰናብቷል” ብሎ ይቀጥላል መልዕክቱ።
“ፔሌ ሲሞት በሚወዱት ቤተሰቦቹ ተከቦ ነበር” ስትል ልጁ ኬሊ ናሲሚዬኖቶ ገልጻለች።
“ላደረክልን ነገር ሁሉ እናመሰግናለን፤ በጣም እንወድሃላን በሰላም እረፍ ስትል” ልጁ ልብን የሚነካ መልዕክት በኢንስታግራም ገጿ ላይ አስፍራለች።
የፔሌ ሞት መላውን የእግር ኳስ ቤተሰብ ያስደነገጠ እና ልብ የሰበረ ዜና ሆኗል።
ከጆ ባይደን እስከ ራሁል ጋንዲ ፤ ከክርስቲያኖ ሮናልዶ እስከ ሊዮኔል ሜሲ ከኪሊያን ምባፔ እስከ ኔይማር ለፔሌ ሞት የሐዘን መግለጫ መልዕክቶች እየጎረፉ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ሜሲ ሮናልዶ ቤካም ከመፈጠራቸው በፊት ፔሌ ነበር፤ ፔሌ የእግር ኳሱ ድንቅ ተጫዋች ነው” ሲሉ ለፔሌ ሕልፈተ ሕይወት ሀዘናቸውን በገለጹበት ወቅት ተናግረዋል።
ተመራጩ የብራዚል ፕሬዝዳነት ሉዊስ ኢግናሲዮ ሉላ ዳ ሳሊቫ “በእግር ኳሱ እንደ እሱ አይነት 10 ቁጥር ተጫዋች በፍጹም የለም፤ እናመስግናለን ፔሌ” ሲሉ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካው ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ እና የፖለቲካ ኮሜንታተር ጆን ሰቲዋርት “ ጓደኛዬ በእግር ኳሱ ላደረከው ነገር እናመሰግናለን” ሲል በትዊተር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት አስትላልፏል።
ብራዚላዊው ኮከብ ኔይማር “እሱ ቢሄድም የሱ ምትሐቶች ከኛ ጋራ ይኖራሉ” ሲል ገልጿል።
“ከፔሌ በፊት እግር ኳስ ስፖርት ብቻ ነበር ፔሌ ግን ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋግሮታል” ብሏል።
ኔይማር ከብራዚላዊው ኮከብ ጋር በ77 ግቦች የብራዚል የምንጊዜውም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።
“የምንግዜውም ንጉስ ደህና ሰንብት” በሚል ሀዘኑን የገለጸው ደግሞ ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው።
“የእግር ኳሱ ንጉስ ትቶን ሄዷል የሱ አሻራ ግን መቼም አይረሳም” ሲል ፈረንሳዊው ኮከብ ኪሊያን ምባፔ ሀዘኑን ገልጿል።
“ የስፖርቱ ትውፊት ንጉሱ በሰላም እረፍ” ጃማካዊው ታዋቂ አትሌት ዩሴን ቦልት በትዊተር ገጹ ያሳፈረው የሐዘን መልዕክት ነው።
“ፔሌ በውቡ ጨዋታ ካየናቸው የእግር ኳስ የምንጊዜም ድንቅ ተጫዋቾች አንዱ ነው፤በዓለማቸውን ስማቸው ከፊት ከሚጠሩ ስፖርተኞችም ይጠቀሳል” ሲሉ የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ገልጸዋል።
“የእግር ኳስ ሰውን አንድ የማድረግ ኃይል በሚገባ የተረዳ እና በተግባር ያዋለ’ ብለውታል የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ ፕሬዝዳንት።
“የእግር ኳሱ ንጉስ በሰላም እረፍ” አርጀንቲናዊው ኮብ ሊዮኔል ሜሲ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ለፔሌ ሐዘኑን የገለጸበት መንገድ ነው።
“የተለየው የተረጋጋው ፍጹሙ ፔሌ መጣ ዋናው ቦታ ሳይለቅ ቆየ፤ ዛሬ ግን ትቶን ሄዷል” ሌላኛው ብራዚላዊ ኮከብ ሮናልዶ የሐዘኑን መልዕክት በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል።
“እግር ኳስ የምንጊዜም ድንቅ አምባሳደሯን አጥታለች” ሲሉ ሕንዳዊው ፖለቲከኛ ራሁል ጋንዲ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት የሐዘን መግለጫ መልዕክት ተናግረዋል።
“ስፖርት የወለደችው የማይገኝ ብርቅዬ ሰው፤ በሜዳው ከሜዳም ውጪ የስፖርቱ ትውፊት” ነው ሲሉ አሞካሽተውታል።
አሁን በርካታ ተጫዋቾች፣ፖለቲከኞች እና የእግር ኳስ አፍቃሪያን ለእግር ኳሱ ምትሀተኛ ሀዘናቸውን እየገለጹ ነው።
ፔሌ የተወለደው እ.አ.አ ጥቅምት 23 1940 በሚኒስ ጌራስ ግዛት ‘ትሬስ ኮሮኬስ’ በተሰኘች ስፍራ ነው።
ዝነኛው ፔሌ ለብራዚል 92 ጨዋታዎችን አድርጎ 77 ግቦችን በማስቆጠር የምንጊዜውም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ከወቅቱ ብራዚላዊ ኮከብ ኔይማር ጋር በጋራ ይመሩታል።
እግር ኳስን በ15 ዓመቱ በብራዚሉ ሳንቶስ ክለብ የጀመረው ፔሌ እ.አ.አ 1958፣1962 እና 1970 ሶስት የዓለም ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችሏል።
ፔሌ በተሳተፈባቸው አራት የዓለም ዋንጫዎች በ14 ጨዋታ 12 ግቦችን አስቆጥሯል።
እ.አ.አ በ1985 በስዊድን አስተናጋጅነት በተካሄደው ስድስተኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዌልስ ላይ ግብ ሲያስቆጥር እድሜው 17 ዓመት ከ 239 ቀን ነበር።
በፔሌ ለአገር እና ለክለብ ባስቆጠራቸው ግቦች ብዛት አሁንም ድረስ ያከራክራሉ።
ኢኤስፒኤን ፕሮፌሽናልና እውቅና የተሰጣቸውን ጨዋታዎች መሰረት በማድረግ አደረጉት ባለው የመረጃ ማሰባሰብ ፔሌ ለአገሩና ለክለቡ 757 ግቦችን ማስቆጠሩን ይገልጻል።
የእግር ኳስ መረጃዎችን እና ክስሰቶችን የሚመዘግበውና የሚያጠናው “ሬክ ስፖርት ሶከር ስታትስቲክስ ፋውንዴሽን” ፔሌ በወታደራዊ ቡድን እና ለብሔራዊ ቡድን ምርጫ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ጨምሮ በ846 ጨዋታዎች 778 ግቦችን ማስቆጠሩን ገልጿል።
ለወታደራዊ ቡድኖች እና ለብሔራዊ ቡድን መምረጫ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች የመጀመሪያ ደረጃ ወይም ይፋዊ እውቅና ያላቸው ናቸው ወይ? የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ ቀጥሏል።
የእግር ኳሱ ምትሐተኛ ፔሌ በስፖርቱ በሰራቸው አስደናቂ ገድሎች እና ታሪኮች በእግር ኳስ አፍቃሪያን እና በመላው ዓለም ሁልጊዜም እየተወሳ ይኖራል።