የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ45 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ45 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 20/2015 በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ45 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ፍሬህይወት አበበ፤ አገልግሎቱ በአሥር ዓመታት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራትና የ2015 የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የአባልነት ምዝገባና እድሳት በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
የዜጎችን የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የጤና መድህን አገልግሎት ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ45 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ገልጸዋል።
ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የአባልነት ምዝገባና እድሳት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
የአባልነት ምዝገባና እድሳቱን በተመለከተ በዓመት አንድ ጊዜ ለተከታታይ ለሁለት ወራት የሚከናወን ስለመሆኑም አስረድተዋል።
በመሆኑም በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች በታኅሳስ እና ጥር ወር የምዝገባና የእድሳት ጊዜ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ይህንኑ አውቆ እድሳትና ምዝገባ እንዲያደርግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።