ቀጥታ፡

ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና ዛሬ ሲጀመር ሁለት የፍጻሜ ጨዋታዎች ተደርገዋል

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 20 2015 የ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር ብሔራዊ የክለቦች ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ዛሬ ከቀትር በኋላ ሲጀመር ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል።

አዲስ አበባ ፖሊስ፣ፌደራል ፖሊስ፣ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ድሬዳዋ ከተማ፣የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ደሴ ከተማ፣ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የውድድሩ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው።

በወንዶች ከ48 እስከ ከ92 ኪሎ ግራም በላይ(92 ፕላስ)፤ በሴቶች ከ48 እስከ 63 ኪሎ ግራም ውድድሩ የሚካሄድባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።

በሻምፒዮናው መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ እያሱ ወሰን፣ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እና የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካዮች ተገኝተዋል።

በመክፈቻው ቀን ዘጠኝ የማጣሪያ እና ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል።

ከ92 ኪሎ ግራም በላይ(92 ፕላስ ወንዶች) የድሬዳዋ ከነማው ይበል መሐመድ የአሜድላውን ሙሉቀን መልኬን በሐኪም ውሳኔ አሸንፏል።

ሙሉቀን በጨዋታው ወቅት ጉዳት ያጋጠመው ሲሆን የዕለቱ ዳኛ ከሕክምና ባለሙያ ጋር በመነጋጋር ቦክሰኛው ጨዋታውን እንደማይቀጥል በማረጋገጣቸው ተጋጣሚው ይበል መሐመድ ጨዋታው ከመቋረጡ በፊት እየመራበት በነበረበት ነጥብ አሸናፊ እንዲሆን አድርገዋል።

በ80 ኪሎ ግራም ወንዶች የአዲስ አበባ ፖሊሱ ሰይፉ ከበደ የኦሜድላውን ናትናኤል ንዋይን በበቃኝ አሸንፎታል።

ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮናው ለክለቦች የውድድር አማራጭ የመፍጠር አላማ እንዳለው የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም በሕንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሴቶች የቦክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ለመምረጥ እንደሚያግዝም ተነግሯል።

ለአራት ቀናት በሚቆየው ሻምፒዮና በወንዶች 90 እንዲሁም በሴቶች 30 በድምሩ 120 ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም