ቀጥታ፡

የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ በሚፈልገው ልክ አልሰራንም፡- የደኢህዴን ተሰናባች አመራሮች

ሀዋሳ መስከረም 21/2011 አገራዊ አንድነትን በማጠናከርና የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ለውጡ በሚፈልገው ልክ አልሰራንም አሉ ተሰናባች የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) አመራሮች፡፡ አመራሮቹ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በድርጅቱ በነበራቸው ኃላፊነት በጥንካሬም ሆነ በጉድለት ለተከናወኑ ተግባራት ሚና ነበራቸው፡፡ በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሬድዋን ሁሴን አገራዊ አንድነቱን በማጠናከር በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር አተገባበር እንደ አገርም ክፍተቶች ነበሩበት፡፡ በድርጅቱም ሆነ በግል በነበራቸው ሚና የስህተቱ አካል በመሆንም ሆነ ስህተቱ በወቅቱ እንዲታረም በተገቢው ባለመስራታቸው ለተፈጠረው ክፍተትም ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ''የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ስር የሰደደ ነው'' ያሉት አቶ ሬድዋን፣ የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በጊዜው ለመፍታት አዲሱ አመራር በትኩረት እንዲሰራበት ጠይቀዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፌጌሳ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት አገራዊ አንድነት ለማምጣት የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ አልነበሩም ፡፡ ክልሉ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኑ ማንነታቸውን፣ቋንቋቸውንና ታሪካቸውን ያረጋገጠ ጠንካራ አንድነት እንዲኖራቸው ከማድረግ አኳያ ብዙ እንዳልተሰራ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ አመራር ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት በማጠናከር ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ በመልካም አስተዳደር ዘርፍ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት አሁን እየታየ ባለው ለውጥ መቀጠል ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሲራጅ፣ በቆይታቸው ለነበረው ክፍተትም ሆነ ጥንካሬ ድርሻ ነበረኝ ብለዋል፡፡ ላለፉት 22 ዓመታት በተለያዩ የሥልጣን እርከን መቆየታቸውን የተናገሩት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ወጣት አመራሮችን በማብቃት ረገድ ጉድለት እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የምርምር ተቋማትና ምሁራንን አደራጅቶ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በጥናት ለመፍታት አለመስራታቸውን በክፍተት አንስተዋል፡፡ የህዝቡን ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የህዝቡን የአስተሳሰብ ደረጃ በሚመጥን መልኩ ባለመፍታታቸው አሁን እየተፈጠሩ ባሉት ችግሮች ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ አዲሱ አመራር ችግሮችን በመፍታት ረገድ ለህዝቡ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ  መስጠት ያሻቸዋል ብለዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም